#ደስታን መጥኖ ስለማስተዳደር። እዮራዊ ምርቃት እንዳይነሳ።
#ደስታን መጥኖ ስለማስተዳደር። እዮራዊ ምርቃት እንዳይነሳ።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀናውን መንፈስ
በውስጤ አድስ።" አሜን። (መዝሙር ፶፩ ቁጥር ፲)
#ምዕራፍ ፳። (20) ተመስገን።
#ለውዶቼ ለአዱኛወቼ ትሁታዊ ጤና ይስጥልኝ።
ለማህበረ - ቅንነት፤ ለቤተ - ሥርጉትሻ ውዶች ህሊናዊ ክብር እና ትሁታዊ ሰላምታ እንሆ። እንዴት አላችሁልኝ። የምር ንፍቅቅ ብላችሁኛል።
የዕውነት የውስጤ ውስጥ መሆናችሁ የሚገለጥልኝ እንዲህ ሳላያችሁ ስስነብት ነው። ስንብቾው እንዴት ነው። እንቁጢ እንዴት
አለፈች?
በመስከረም በርካታ ወገኖቻችን ልዩ የበዓል ሴሪሞኒ አላቸው። በዚህ አጋጣሚ እንኳን አደረሳችሁ። በዘርፋ ደካማ ነኝና፤
ሳላስታውስ ስቀር እለፋኙ።
በተረፈ 2019 ሰላም በእያንዳንዳችን ቤት የሚገባበት ያድርግልን። አሜን።
1) #ደስታና ሐሤት ምን እና ምን ናቸው በሥርጉዬ - ፍልስፍና።
1.1) ደስታ ምድራዊ፤ ሰው ሠራሽ፤ ጊዜያዊ እና ቆይታውም የማይታመን፤ ትነት ሊገጥመው የሚችል።
2.2) ሐሤት ሰማያዊ እና አማኑኤል ሠራሽ ገኃዱ ዓለምንና መንፈሳዊውን ዓለም የሚያገናኝ ቋሚ እና ዘላቂ ድልድይ።
የምድራዊውን ደስታ በሚመለከት የመጀመሪያ ጹሁፌ የመቀሌ በመከላከያ ሥር ገባች ርችት፤ ፈንጠዝያ፤ ፌስታ ጊዜ
ነበር የፃፍኩት። ከዛም በኋላ በተለያዬ ጊዜ የተንጠራራ የፌስተ ድለቃ ሳስተውል በልክ ያዙት በማለት ማሳሰቢዬ አልቀረም።
2) #ለምን?
2.1) ባለ ደስታው ተጨማሪ ደስታ ሲያገኝ #መደርደሪያ እንዳያጣ፤ ማስቀመጫው፤ እንዳይጠበው።
2.1) ባለ ደስታው ደስታው እየራቀው ሲሄድ ተስፋ ቆራጭ ሆኖ ለሥነ - ልቦና #ህመም እንዳይዳረግ።
2.3) ፈጣሪ የበዛው ፈንጠዝያ ተመልክቶ #ምርቃት እንዳያነሳ።
የሚያስፈራኝ ህዝብ የሥነ - ልቦና ህመም ተጠቂ ሲሆን ነው። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ለ130 ሚሊዮን ህዝብ ስንት
የሥነ - ልቦና ሃኪም አላት? ይህንንም እሰቡት እንደማለት።
በእነኝህ ምክንያቶች ደስታን በልኩ፤ መጥኖ መያዝ የተገባ ነው። ለየትኛውም ህይወት፤ የአኗኗር ዘይቤ ሁሉ ቢፈቀድልን፤
ብንችል በልክ፤ በመጠን ሲሆን ይበጃል። ዛሬ ጥሬጨው (የጎንደሬ አማርኛ ነው) ተገዝቷል ተብሎ ሳይመጠን አይዶልምና።
3) #መከፋት እና የደስታ ገጠመኝ።
በመከፋት ጥንስስ፤ ዕድገት እና ጉልምስና ውስጥ መከፋትን የሚክስ አጽናኝ ሁነት ከገጠመ ደስታ የስሜት ረቂቅ
ህዋስ ነውና ይፈጠራል። እናም የመንፈስ መረጋጋትን ያሰርጣል። ግን በልክ መያዝ እንደ ተጠበቀ ሆኖ።
4) #ምኑ? እኮ ምኑ?
በጦርነት ውስጥ ምኑ ደስታ ሊፈጥር እንደሚችል ደርሶብኝ ስለማያውቅ ጣሙን አላውቀውም።
4.1) ጦርነት የዕንባ ዋናተኛ ነው።
4.2) የበቀል ዘር ነው። የቂም ችግኝም ነው።
4.3) የጥላቻ መፈልፈያ ካንፓኒ ነው።
4.4) የክፋ ሃሳብ መራቢያ አካል ነው።
4.5) የመለያዬት ግንብ ነው።
4.6) የመጠራጠር ጣዖት ነው። ምኑ ደስታ እንደሚሰጥ የማይገባኝም ለዚህ ነው።
#ዕውነቱን ልንገራችሁ።
እኔ ያደግኩት በጦርነት ቀጠና በምትታወቀው በእቴጌ ጎንደር ጎንደር ከተማ ነው። ቤተሰቦቼም ተወልደው ያደጉት ከዛ ነው። ያደኩት የጦርነት ስጋት ተመግቤ ነው። እናም ፈጣሪ የሰጠኝ የውስጥ ሰላሜ ታውኮ በሰቀቀን፤ በፍርኃት፤ በራድ ውስጥ ሆኜ ላደግኩት ለእኔ ለስርጉትሻ ጦርነት ተናፋቂ፤ ተወዳጅ፤ ደስታ ፈጣሪዬ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም። በዕውን አይቸዋለሁ። ህይወቱንም ኑሬበታለሁ።
አንድ የደቡብ ኢትዮጵያ ሊቅ በአንከር ሚዲያ ቃለ ምልልስ ያደረጉ "የምሥራች" ሲሉ አዳመጥኩ። "ጦርነት የምሥራች" አይደለም። ከቃሉ
ጀምሮ። ለነገሩ እራህብን ለማያውቀው ራህብ ምንድን ነው ተብሎ ሲጠየቅ ራህብ ምንድነው ብሎ መልሶ ይጠይቃል። አያውቀውም
እና። አንድ አክርማ እና የዳጉሳ ቡቃያ ለማያውቅ ሰብ የትኛው ዳጉሳ፤ የትኛው አክርማ ተብሎ ቢጠየቅ አያውቀውም።
ጭምቱ ደቡብ የሚከፍለው መስዋዕትነት፤ ይሁን #ሰማዕትነት የለም። እንደ አገር በመከላከያ ሠራዊት ከሚታደምበት በስተቀር። መሬቱ
በባሩድ፤ በድሮን፤ በሚግ፤ በመድፍ፤ በመትረየስ #ነዶ አያውቅም። ከድል ማግሥት ተከብሮ ተጠቃሚ ግን ደቡብ ነው።
ጭምቱ ደቡብ ልጆቹ በገፍ ከፋኝ ብለው፤ #አንጋች ሆነው የተጋፈጡት አንድም ሥርዓት የለም። ኢህአዴግ ሲገባ የተሞሸረው ተከብሮ ነው። ጠቅላይ ሚ/ር ልጅ ያደረሰው በሰላም ልጁን ስላስተማረ ነው። የጠቅላይ ሚር ቤተሰብ ተምረው በቤተ- መንግሥት የሠርግ ወግ ያገኙት በሰላም ዕድሜያቸው ሳይስተጓጎል መማር ብቻ ሳይሆን ከአሰቡት በልቅና ስለደረሱ ነው። በማን ማገዶነት? ይህን ሁልጊዜ አንጋች የሆኑት #ስሜነኞች በተለይ ትውልዱ ይገምግመው።
በጸረ ህወሃት ትግል እና ስኬት ማን - ተገበረ? ማን - ተማገደ? ማን ቅራኔ ውስጥ - ገባ? ማንስ የበቀል ማገዶ - ሆነ? ያላችሁበት ስለሆነ መዝኑት። ህወሃት መንበረ ሥልጣኑ ሲነቃነቅ ለሁለተኛ ጊዜ ዕጩ ጠቅላይ ሚ/ ር ጭምቱ ደቡብ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን አቅርቦ ነበር ጭምቱ ደቡብ።
ሁለት ድምጽ ብቻ ለኦህዴድ የሰጠው ጭምቱ ደቡብ፤ ሙሉ 45 ድምጹን፤ ለጠቅላይ ሚ/ ር አልወዳደርም ብሎ እራሱን
#ደፍጣጩ ካንስል አድራጊው #አንጋቹ ብአዴን ለኦህዴድ ክርስቶስ ቀራንዮ ላይ ለሰው ልጅ የሰጠውን ፍቅር ሰጥቶ፤ ሰማዕትነት ተቀበለ። የህወሃት የእስር ቤት ተጋዢም ያው መከረኛ ነበር።
ይህ ብቻ አይደለም ስለተፈለገ ለውጥ የለም። ስለተመኜህ ዕድል የለም። የግሎባሉ የፈቃድ መሐተም ያስፈልግ ነበር። እግዚአብሄር
ከሠራው ቅንነት በላይ የሆኑት የአማራ ልጆች ህወሃት ከተፈጠረበት ዕለት ጀምሮ ተጎጂወች ስለነበሩ ለዛ ለጨነገፈው፤ ለከሰለው፤ ላልተደገመው ይሁን ላልተሰለሰው ጠቀራ "ኢትዮጵያዊነት ሱሴ" ታመኑ - ፈቀዱም። እናም ኦህዴድ ዕድል ተሰጠው። በዚህ ሁሉ ጠብ የምትል የሰማዕትነት፤ የማገዶነት፤ የግጭት ሁነት በጭምቱ ደቡብ የለም። አልነበረም።
አንድ ሁለት ሊቃናቱ የፊት መሪ ሊሆኑ ይችላሉ። በየትኛውም የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት። ህዝቡ ግን እንደ ህዝብ ልጆቹን ያስተምራል፤ ይድራል ይኩላል። የሚስተጓጎል የኑሮ መስመር የለም። ተከብሮ፤ ተወዶ፤ ተናፍቆ የገጠመኞች የድል እርከን ሁሉ ጭምቱ ደቡብ ተጠቃሚ ነው። አይጠረጠር፤ #አይመነጠር።
ኦህዴድ ሥልጣነ - መንበር ሲረከብ፤ ከዚህ ግባ የሚባል መስዋዕትነት ያልከፈለው ደቡብ በተለምዶ "ኦሮሞ፤ ኦሮሞ" የሚል ድምጽ
ይጎላል እንጂ፤ የኦሮማራ መሪወች #ስምጠት ተበይኖባቸው በካቢኔው 50+ ደቡብ ነው። የጠቅላይ ሚር ጽህፈት ቤት ህሊና ደቡብ ነው፤ የፓርላማው ቁልፍ ደቡብ ነው። የደህንነቱ አከርካሪ ደቡብ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚ/ር እና ፍትህ ሚ/ር ደቡብ ነው። ትምህርት
ሚ/ር ደቡብ ነው። ፕላን ደቡብ ነው፤ ግሎባል ጉዳይ ሰብሳቢ ደቡብ ነው። ክህሎት ሚ/ር ደቡብ ነው። የአብይዝም ዘመን ልዩ ማጣፈጫ ኮረሪማ ደቡብ ነው።
የወደፊቱ ደግሞ እንዳያመልጣቸው ነው የስሜነኞች የህብረት ማገዶነትን ለእኛ "የመስቀል፤ የአዲስ ዓመት ሥጦታ፤ የምሥራቻችን ነው" ሲሉ የምናደምጠው።
#ለምን የየዘመኑ ዕድል ቀዳሚ ተጠቃሚነት በክብር ሊሆንላቸው ቻለ?
እኔ የደረስኩበት ዕሳቤ ደስታቸውን በልክ የመያዝ አቅም አላቸው ብዬ አስባለሁኝ። ሰላማዊነትን ዶግማቸው ያደረጉ ይመስለኛል። በሌላ በኩል ዕድሉ ሰተት ብሎ እንደሚመጣላቸው ባለቀ ሰዓት ስለሚያውቁ ለነዲድ፤ ለመውደም፤ ለሰቆቃ በራቸው #ዝግ ነው። ሰሞኑን አላማጣን እሰቡት እናት ከልጇ፤ አራስ ልጅ ከእናት ጡት የተለዩበትን፤ ደቡብ የተመጠነ የቤተሰብ ፌስታ ላይ ነው ያለው። ልጆቹም ያለ ስጋት፥ ያለ ሰቀቀን ወደ ትምህርታቸው ……
ብልፄው ቢያሸንፍ ይሁን ቢሸነፍ ጭምቶቹ ደቡቦች በቅተው፤ ጸድቀው፤ ስለሚጠብቁ ተመራጭ ናቸው። ለምን ይገበሩ? ይህ ጉዞ ለእኔ የዊዝደም ጉዞ ነው። ይህ ጉዞ የትውልድ ኃላፊነትን የመወጣት የብልህነት ጉዞ ነው።
#ጦርነት ለእርካታ አይደለም።
ጦርነት በብዙ ሁኔታ ይከሰታል። ገፊ ምክንያቶች ይኖራሉ። ግን ለገፊ ምክንያቶች ጥሞና እና ጠሎት፤ ብቃት እና አደብ ያስፈልጋል። የጦርነት ይሁን የግጭት ፈላስማወች አዋቂወች "ህጋዊ" እና "ህገ ወጥ" ይሉታል። ህጋዊ ይሁን ህገ - ወጥ ማገዶው የሰው ልጅ ነው።
መኖር ተገብሮ። ዕድሜ በነዲዲድ ነዶ፤ ክልትምትም ተብሎ፤ ቅጠል ተለብሶ፤ ቅጠል ተበልቶ ነው የሚከወነው። የተማገደው
ያልቃል። ይጎሳቆላል። ሊጠፋም ይችላል።
ከድል መልስ ተጠቃሚው ራሱን የጠበቀው ብቻ ይሆናል። ቅራኒ ውስጥ ያልተዶለው ይሆናል። ይህ ተፈለገም // አልተፈለገም የሁኔታው አስገዳጅነት የሚፈጥረው የሃቅ እንክብል ነው። ለማን ይማገዱታል? ለማን ይሞትለታል?
ሺወች ትናንትም ዛሬም እየተፈናቀሉ ነው። ሺወች እየቆሰሉ፤ አካላቸውን እያጡ ነው። በድኃ አገር ዕዳው ተከፍሎ ሳይጠናቀቅ ፕሮጀክቶች የሳት ራት እየሆነ ነው። መጓጓዣ እየተስተጓጎለ ነው። ተማሪወች አይደለም መማር #መኖር አልቻሉም። ትውልድን
በማክሰል ደስታ እንዴት ይመጣል?
#ፍርኃት እና ትውልድ።
ፍርኃት ሲያድግ፤ አብሮ ሲኖር በሽታ ነው። በራስ መተማመንን ይፍቃል። በራስ መተማመን የሌለው ትውልድ የአገርን አደራ
እንዴት የመረከብ አቅም ይኖረዋል? ትዳር መመሥረትን ሳይቀር ይፈራል። የቤተሰብ ምሥረታ ወና ይሆናል። አገር የታጨላት ያ
እና ይህን መሰል #ጢስ ዕጣ ፈንታ ነው። ይህ ያስቃል? ይህ ደስታን ይሰጣል? ይህ ርችት ያስተኩሳልን? መዝኑት?
#ቃጠሎ ሲናፈቅ - ነገ እንደምን ይታሰብ?
የትምህርት ቤት ቁሳቁስ ማገዶ --------ሲሆን?
ሆስፒታሎች --------------ሲነዱ?
ህዝብ በገፍ------------ ሲፈናቀል?
የሚወዱት ----------ሲለይ?
በስንት መዋለ ንዋይ የተሠራ አውሮፕላን ማረፊያ ለባሩድ ------ሲታጭ?
የነዳጅ ጫኝ ቦቴወች እሳተ ጎመራ---------- ሲታዘዝባቸው?
#ጦርነት ምክንያታዊ ነውን?
ሊሆን ይችላል። ግን ለትውልድ አትራፊ አይደለም። መኖሩን ስለሚቀማው። ስለሆነም ተው፤ አታዳፈሩት ልል እፈልጋለሁኝ።
ትርፍ ከምን -----መዳረሻ?
አጤ ጦርነት አተረፍኩ ካለ የሚያተርፈው ጢስ፤ አመድ፤ እሬሳን ብቻ ነው።
በተጨማሪም ቂም፤ በቀል፤ ጥላቻ በገፍ ማምረት።
#የሥርዓት ሹም ሽር ምኞት።
በጦርነት አይሳካም። ቢሳካም በረከት የለውም። ህወሃት ፈቅዶ መንበሩን የለቀቀው በብዕር እንጂ በባሩድ አልነበረም።
#በአየሁት ሃቅ ልቋጨው።
የህወሃት እና የደርግ ጦርነት በጎንደር ያዬሁትን ነው እምነግራችሁ። ውሻ የሰውን ልጅ ጭንቅላት ይዞ ሲመጣ በዓይኔ አይቻለሁኝ።
ጦረንተን ድሮም አልፈቅደውም፤ ይህን ካየሁ በኋላ ደግሞ ሳስበው ይሰቀጥጠኛል። በዚህ ዙሪያ ደረታቸውን ነፍተው የሚናገሩ፤
የሚተነትኑ፤ የሚያብራሩ ሰወች ሳይ ሰው ሆነው መፈጠራቸው ያሳዝነኛል። ነገሩ ከበሮ በሰው እጅ ነው። ይቁነጠነጣሉ፤ እፍ ግብ ይላሉ፤ ለእነሱ የተንደላቀቀ ኑሮ እራፊ የለለው ገበሬ እና ኑሮው ይማገዳል።
/// ጦርነት የጫጉላ ሽርሽር አይደለም።
//// ጦርነት የሠርግ ቅልቅል አይደለም።
///// ጦርነት ጭካኔ ሰልጥኖ የሰው ልጆችን የሚፈጅበት፤
///// ለመሬትም ነዲዳዊ ላርባ የሚታዘዝበት ሰው ሰራሽ መቅሰፍት ነው።
/////// እርግማንም።
//////// ላርባዊ ቅጣትም ነው።
///////// የእዮራዊ ምርቃት መነሳትም።
የሰማይ ምርቃት መነሳትን መናፈቅ አይገባም። መስዋዕትነትን የሚቀንስ ብዙ በጣም ብዙ መንገድ አለ።
ስለሆነ በጥሞና፤ በአርምሞ፤ በተደም፤ በፆም በጸሎት በድዋ ወደ እዮር አቤቱታ ማቅረብ ያስፈልጋል።
በአዲስ ዓመት፤ በዘመን መለወጫ፤ በመስቀሉ ብርኃን ጦርነት --------?????? ------?????
ምርኮ፤ ሽንፈት፤ ድል ሁሉም በሰው ግብር የሚሰሉ ገጠመኞች ናቸው። ለጢሳዊነት ተመራጮች ደግሞ
አማራ ክልል እና አፋር? እን ---- ቆ ---- ቅ ----- ልሽ። ህም በዕም!
መሬት አዝዕርት ስታበቅል ተመጋቢው ነገ የትውልድ ህመምን ያረገዘ ይሆናል። ይህ ምድራዊደስታን፤ ሰማያዊ ሐሤትን በምን
አቅሙ ሊያዋልድ ይችል ይሆን?????
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
29/09/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
See less
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ