#አናባቢ (Vowel)። ትዳር መጽሐፍ ነው የሚነበብ።

 

#አናባቢ (Vowel)። ትዳር መጽሐፍ ነው የሚነበብ።
 
"ቤት በጥበብ ይሠራል። በማስተዋል ይጸናል።"
(መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፳፬ ቁጥር ፫።)
 
 
 
ይህ እስከ ዛሬ ከሰማሁት ቃለ ምልልስ በላይ ነው። የሚስትነት #ተፈጥሯዊ ማንነት አናባቢ ሆኗል። እንዲህ የቀረብኝን ግን የተመሰጠረ ተራራ ዕጣ እና ጥሪ ውስጡ ያደረገ ሰብዕና ባገኝ ምን ልል እንደምችል አላውቅም። 
 
#የአገላለጽ ዘይቤ።
 
የንግግር ጥበብ ጥበብ ነው። ጥበቡ በመማርም ይገኛል። ሲታደሉት። ንግግር መማሩ ይሁን የማስተማር ዕድል ያለውም ቢሆን የመናገር አቅም ላይኖረው ይችላል። ርትዑ የመሆንም ጸጋ በዚህ ቃለ - ምልልስ አዳመጥኩ። ንግግር ጥበብ ነው። ጥበቡ በሥልጠና ሲታገዝ ወደ ክህሎት ያድጋል። መስጦኛል የአርቲስት ወ/ሮ አምለሰት የአመላለስ አቅም። አቀራረቡ ግልጽ እና አጭር፤ ግን ውስጥን የማንኳኳት አቅሙ - ገድለኛ። ደርባባ፤ ምራቁን የዋጠ አቅም። 
 
#ሳጉ ብዙ ያስተምራል። 
 
ዕደለኛ ነው ቴዲ። ልኩ የሆንሽ ደልዳላ እመቤት። ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ውጭ ያሉ ቤተሰቦቼ እናቴን በስልክ እንዳገኝ አደረጉ። ስለምፈራ የውጮችንም የአገር ውስጦችንም እናቴን ጨምሮ በስልክ አላገኛቸውም። በውነቱ የመኖር ነፃነታቸው በእኔ ምክንያት መስተጓጎል እንዳይደርስበት በብርቱ እጠነቀቃለሁኝ። 
 
ከባሩድ ምኞት ጋር እኔ የለሁም። ከየትኛውም የፖለቲካ ተቋም ነፃ ነኝ። አንዱም ፈተና ይህው ነው። ግን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዕርንም ፈሪ ነው። እና ጠንቁ ለቤተሰብ እንዳይደርስ ናፍቆት አገላብጦ እሽት እያደረገኝ ያው ለኢትዮጵያ ተብሎ ቤተሰቦቼን ቀጣሁኝ። ናፍቆትን ተጭኜ ድምጼን ለቤተሰቤ ነፈግኩኝ። ለደህንነታቸው ስል። ብዕር እና ብራና ብቻ ነው ያለኝ።
 
የሆነ ሆኖ ከብዙ ጊዜ በኋላ እናቴን በስልክ ሳገኛት #ጸልይልኝ አልኳት። "#ሱባዔ ላይ ላለ ነፍስ?" ብላ ደግማ ጠየቀችኝ። የማይነገሩ ብዙ ነገሮች አሉ። ቴዲ መኖሩ #ሱባኤ ላይ ነው። ይህን የሚረዳ መንፈስ አናባቢ ነው። ኢትዮጵያ - ኢትዮጵያዊነት - ሲኖርበት ወጀብ አለው። ወበቅ አለው። ኢትዮጵያን ለመፈወስ ቢባልም ውስጥ ግን ቀንጣ አቅም ይሳደዳል፤ ይገለላል፤ ከዚህም ያለፈ ጥቃት ይመጣል።
 
"ጠንካራ ሴት መባል ስያሜው ጫና አለው"ቴዲ በአንቺ አንደበት እንዴት ይገለፃል!! ቆይታ ከአምለሰት ጋር በአዲስ አቀራረብ#amleset #season2
 
ዕውነት ከባዱ የህይወት ፈተና ነው። ነፃነት ሌላው ተራራ አመክንዮ ነው። አቃፊነት አሳር ነው። ለአገር ሳይሆን ለአንድ ሰብዕና መቆርቆር ግን የጽድቅ መንገድ ነው በአንድ ወቅት። በሌላ ወቅት ደግሞ መሳደጃ፤ ባን መደረጊያ ይሆናል።
 
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለሰው ልጅ የተሰጡ እዮራዊ ጸጋ እና በረከቶች፤ ምርቃት እና ነፃነቶችን ተቀናቃኝ ነው። አንዲት ኮቢ ገዝቶ ያላስተማረ ግን ዕድል ቀንቶት መንበር ላይ ቁብ ላለ ሰብዕና ተንበርካኪ መሆን ካልቻለ ትናንትም ፈተና፤ ዛሬም ፈተና - ነገም ፈተና ይታጫል።
"#ኑር" ብሎ ፈጣሪ አላህ የደነገገው ድንጋጌ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አይኑርህ ብሎም የአምልኮ፤ የጸጋ ስግደት የሚሹ መንፈሶች የኢትዮጵያ ፖለቲካ በየዘመኑ ይፈጠር እና፤ የየዘመኑ ትውልድ በጭንቀት፤ በስጋት እንዲኖር ይገደዳል። ባለፈም ሰማዕትነት አለበት። 
 
ለኢትዮጵያ ሥም የለሽ ፖለቲካ ተመራማሪ ያስፈልገዋል። ይህ ቃለ ምልልስ በአጽህኖት የሚያስተምረው ይህ ነው። ያለው በመንፈስ አቅም፤ ያለው በፋይናንስ አቅም። ያለው በኢኮኖሚ አቅም። ያለው በተወዳጅነት አቅም። ያለው በተቀባይነት አቅም። ያለው በተፈሪነት አቅም። ያለው በተወዳጅነት አቅም መኖሩ ግን ባልተቃናው፤ ጊዜ ባላስተማረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጥምልምል፤ ፍትልትል ባህል እንዲህ በቁም እስረኝነት መኖሩ መሰቃየቱ ሊያሳስበን ይገባል።
 
የሚስት - የእናት - የእህት - የአክስት - ደስታ፤ ፍሰኃም አብሮ ይወቃል። ለልጅም ይደርሳል። ያ ትንሽዬ ልጅ እናት ሲደክማት፤ ሲታክታት ግን ልጆቿን ልታስደስት እንዳይጎልባቸው ስትባትል አዬ። ተመለከተ። ደርሻለሁ። እርፍ በይልኝ አለ። በዚህ ውስጥ ረፍት ላይ የሚጎልባቸው መንፈስ አለ አባት አብሮ ላይሄድ ይችላልና። በዛ ላይ ----- ጉዞው አለ። ድካሙ አለ። ወጪው አለ። ግን አሁንም ደስታው ሙሉ አይደለም። የቀረ የጎደለ አለ።
 
ለዚህም ነው አናባቢ ያልኩት። ዕድለኛ ብንሆን የቤተሰብ፤ የህፃናት፤ የሴቶች፤ የልጆች የመንግሥት አካላት ሊሠሩት የሚገባ ተግባር ይህ ነው። ሰው በአቅሙ ልክ የቤተሰቡ ደስታ ካለ ስጋት፤ ካለ ፍርሃት፤ ካለ ጥርጣሬ እንዲከወን የህሊና ለውጥ ላይ ሊሠሩ ይገባቸዋል። ሴቶች ወደ መሪነት ሲመጡ ይህን የትውልድ ቀረፃ እና ኃላፊነት በእርጋታ እና በማስተዋል ሊቀይሱት ይገባል።
 
የህዝብ የውስጥ ሰላም። የህዝብ የመኖር ነፃነት ላይ ሥራ ሊጀመር ይገባል። ከታች እስከ ላይ፤ ከላይ እስከ ታች ሰውኛ፤ ተፈጥሮኛ ስፕሪት ሊፈጠር የሚችልበትን ሁነት ማመቻቸት ያስፈልጋል።
 
መዋቅር ብቻውን፤ የኃላፊነት ደረጃ ብቻውን፤ ሹመት ሽልማት ብቻውን ትውልድን አገርን ታሪክን አደራን ሊያስቀጥል አይችልም። የማይነገሩ የውስጥ ጭንቀቶች፤ የታፈኑ የመኖር አሳሮችን ፈልፍሎ ማግኜት፤ የቆሰለውን መጠገን ይገባል። ነፃነት በነፃነት አገር ዕውን ሊሆን ይገባል።
 
#እሜቴ ነፃነት እንደምን ከርመሻል? ከአምናው ሸክማ ሸክምሽ ዘንድሮ ………?
 
መኖር ---- በነፃነት፤
መማር --- በነፃነት፤
ማግባት መውለድ ---- በነፃነት፤
መጸለይ --- በነፃነት፤
ማሰብ --- በነፃነት።
መፃፍ ---- በነፃነት፤
መዘመር ---- በነፃነት።
ሰዓሊነት ---በነፃነት።
ግጥመኛነት --- በነፃነት።
መዝፈንም --- በነፃነት።
 
ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ብዙ መዋቅር፤ ብዙ ሹማምንት አለ። "ለህዝቤ ታማኝ ለመሆን" የሚል ቃል ሰሞኑን አዳምጣለሁኝ። ፈውስ አምንጪ ግን የየቤቱ መኖር እና አጋጣሚው ግን የታሠረበት ገመድ አለ። ወይንም የተበተበ ክር አለበት። ያን ማፍታት ያስፈልጋል። ደፍሮ በችግሩ ላይ ተወያይቶ መፍትሄ ማመንጨት ያስፈልጋል። 
 
በአገርም --- ስደት፤ በስደትም ----- ስደት ቀማሪው፤ ያልተገራው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀመር ነው። ይህን ተሸክሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነገ እንዴት ይታሰብ? #ማለዳ እንዴት - ይታሰብ? ንጋትስ እንደምን ይታጭ? ጸሐይ እንደምን ---- ትታሰብ? ፕሮጀክት ማቀድ እና መፈጸም ብቃት ነው። ነፃነትን እንደ አንድ ፕሮጀክት ይዞ አቅዶ፤ መፈጸም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢሊቶች ተግባር ሊሆን ይገባል።
 
የኢትዮጵያ ፖለቲካ አመክንዮ ህሊናን #ሊገዛ እንዲችል ሊሠራበት ይገባል። ሰኔ 16/2010 ዓም እኮ ፕሮፖጋንዲስት አልነበረውም። ጥራት ያለው አመክንዮ ነው የጠራው። ጭምቱ ማህበረሰብ አንገቱን ደፍቶ በየዘመኑ የሚጠብቀው፤ የሚመኜውም ነፃነት ቃሉን ሳይሆን መሆን የቻለበት ነፃነት፤ መሆን ያስቻለበት የነፃነት ብቃታዊ አቅምን ሁነት ዕውናዊነት ላይ መሥራት በእጅጉ ያስፈልጋል።
 
አገረ መንግሥት ለህዝቡ ጥግ፤ ዋርካ መጠለያ እንጂ #የሚፈራ ሊሆን አይገባም። መንፈስን ሊያግት አይገባም። ይህ ውጭም አገር ውስጥም ሳየው፤ ስታዘበው የኖርኩት የሃቅ እንክብል ነው።
 
ዘላቂ መሻቴ #ካለጠባቂ የሚሄድ መሪ ሲናፍቀኝ ነው የኖረው። ህዝቡ እራሱ የመሪው ጠባቂ የሚሆንበት ዘመን። ይህ የሚገኜው ለህዝብ የአኗኗር ዘይቤ በሚሰጠው የነፃነት ልክ ሊሆን ይገባል።
 
#ላሂው ያማረበት።
 
ውስጡ ያማረበት ትዳር በቃለ- ምልልሱ አየሁኝ። የትዳር አጋርን በአክብሮት፤ በትህትና መያዝ። ሲቆጣም የውስጥ አቅም አድርጎ መቀበል። ተፈጥሯዊ አቅሙ ይስባል እንደ ማግኔት።
 
የትዳር አጋር ለአጋሩ አቅም፤ ክህሎት፤ ችሎታ፤ ትጋት፤ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ዕውቅና መስጠት ሥልጣኔ ነው። የማይገኝም። ሺ ሚሊዮን ቢዲዮ ሲያደምጥ ውሎ የሚያድር የእራስን አካል፤ እህት ወንድም ጥረትን ለማድመጥ የማይፈቅዱ #ልሎች አሉ። በዚህ ቃለ ምልልስ የተረዳሁት የማንነት ሥልጣኔ ልዕልና በልቅና በጎጆ አምሮበት ነው።
 
በጆሲ ቤት የመጀመሪያ ቃለ ምልልስ አዳምጬ ነበር። አልፎ አልፎም እንዲሁ። በዚህ ቃለ ምልልስ ግልፅ፤ ቀጥተኛ፤ ተፈጥሯዊ የበቃ አቅም አይቸበታለሁኝ። ትዳርን በሙሉ አቅም መምራት ህይወቱ ለሌላም ትምህርት ነው። የተባረከ ዕውቀትም።
 
 
ለእናት ትርጉም የላትም። የማህጸኗ ምርቃት ፍሬ ልጅም ትርጉም የለውም። ከጽንሱ ጀምሮ። ከባጉም ባጉም እስከ ታዳጊ ወጣት የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ለወላጅ ይከብዳል። አንዳንድ ጊዜ እናት የአባትንም ድርሻ አክላ፤ ሌላ ጊዜ አባትም የእናትን ድርሻ ደርቦ የሚረዳዱበት ጎዳና አለ። ይህ ለልጆች ሌላ የህይወት ሌሰን ነው።
 
በዚህ የሂደት ሽርሽር ድካም አለ። ልጅ ደርሶ ድካሙን ሼር ለማድረግ ልጆች ሲፈቅዱ #መመረቅ ነው። ምርቃቱ ለዛሬ ብቻ አይደለም። ለነገው የቤተሰብ አመራር #የፊደል ገበታ ነው። የተመሰጠረውን፤ ግን የማይነገረውን የእናት ድካም ለመጋራት መፍቀድ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው። የተባረከ ትውልድ መሠረቱ ከመሠረቱ ይጀምራል። "የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ" እንዲሉ።
 
በዚህ የመሆን ጉዞ ያዬሁት ሌላው ብልህ ጉዳይ ልጆች ነገን #እንዳይፈሩት ህሊናቸውን ያሰናዳል። ትዳር መመስረት ብቻ ሳይሆን ሚስት እናት ስትሆን ያለባትን ኃላፊነት እየተከታተሉ ሼር ማድረግ ባህላዊ፤ ተለምዷዊ ለማድረግም ይረዳል። ይህ የመታደል አማርኛ ነው።
#ሳቅ ስለማዋጣት።
 
ለየትኛውም ግንኙነት ሳቅ ዕውነተኛው የተፈጥሯዊነት መንበር ነው። "ይስቅልኛል" ውስጡን - የውስጡ - በውስጥነት ሲገናኝ ደቂቃዋ አትባክንም። መኖርን አሰልጥና ሰናይን ትናኛለች። ተቆጥቦ፤ ተከድኖ የተቀመጠው የማሳቅ አቅም ለእኛም ይድረሰን ብለናል አመልዬ እቴጌዋ። 
 
ተብዓት ውስብስብ ነገር አይፈልግም። ቅልል ያለ፤ ፈታ ያለ፤ ግልጽ እና አጭር አመክንዮ ብቻ ተብዓታን ይፈልጋሉ። አሰልቺ፤ ሸክም የሚበዛበት፤ ግልጽነት የጎደለው ጉዳይ ለተባዕት እንደ ዕዳ ነው የሚዩት። ስልቹም ይመስሉኛል። ስለዚህም ምርጫቸው ቀለል ያለ የህይወት መስመር ከሆነ ለዛ ብቁ ሆነ መገኜት ከሴቶች ያስፈልጋል።
 
አማካሪ ተብዕት ሲሆን፤ አለቃ ተብዕት ሲሆን፤ መምህር ተብዕት ሲሆን ብዙ ነገሮች ቀላሎች ናቸው። ቀላል አቀራረብ ከኖረ። ለየትኛውም የተብዕት አቅም ቀላል አቀራረብ ተመራጭ ስኬታማ ያደርጋል። ለሦስት ጉልቻም እንዲሁ። በዚህ ቃለ - ምልልስ ያዬሁት ጠቃሚ ሁነት የውስጥነት ኃዲዱ የተዘረጋበት ተፈጥሯዊነት በምፈልገው ልክ አግኝቻለሁኝ። 
 
#ፎርማቱ እና ኃላፊነቱ።
 
የሚዲያው ፎርማት እና ኃላፊነቱን ሁላችንም እየተከታተልነው ነው። ሁሉንም ባይሆን የተወሰነ ነገር አደምጣለሁኝ። የለቱ ቃለ ምልልስ ያደረገው ሰብዕና ለስላሳ፤ ምቹ፤ ዲስፕሊንድ፤ ትሁትና በዕውነተኛ አክብሮት የተቃኜ ሂደት አየሁኝ። ይህም በራሱ በመሰል ሚዲያ ለሚሠሩ ሁሉ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ብዬ አስባለሁኝ። 
 
ልጆች ከሚሰሙት ይልቅ በሚዩት ያምናሉ፤ ይማራሉም። የትውልድ ግንባታ በየጥቃቅኑ ፌርማታ #የታረመ አንደበት፤ ተግባር መፈጸም ይገባል። ልፋቱ ካልቀረ ትውልድ እየታሰበ ይሁን ባይ ነኝ። ገና #ላልተጸነሱት ሁሉ አስቦ ተግባርን አህዱ ማለት ይገባል ባይ ነኝ። 
 
ትዳር #መጽሐፍ ነው። የዕውቀት ኃላፊነት መሰልጠኑን በትዳር መመዘን ይቻላል። የማህበረሰብ ምንጭም ትዳር ነው። አገርም ከትዳር ይነሳል። ትዳር እራሱ የአገር አስተዳደር ነው ላወቀበት - ለተሳካለት - ላደለውም። 
 
ውዶቹ ክብሮቹ እንዴት አረፈዳችሁ? እንደምንስ ዋላችሁ።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሸበላ ጊዜ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
12/10/2026.
ዕውነት ወጌሻ ወይንም ጋራጅ አያስፈልገውም።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
See less


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።