የኢትዮጵያ ፖለቲካ መጠጊያ እንጨትን #አዘውትሮ ባያማትር። ቅንነት ማኒፌስቶ ይሁን።
· የኢትዮጵያ ፖለቲካ መጠጊያ እንጨትን #አዘውትሮ ባያማትር።
· ቅንነት ማኒፌስቶ ይሁን።
#ምዕራፍ ፲፭
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
ጤና ይስጥልኝ ማህበረ አወንታውያን፦ እንዴት አደራችሁልኝ? ደህና ናችሁ?
የኢትዮጵያፖለቲካ መጠጊያ #እንጨት አዘውትሮ ፍለጋ ከሚባዝን እራሱን #ችሎ መቆመን ቢለማመድ ጥሩ ይመስለኛል። እንጨት እኮ #ምስጥ ይበላዋል፤ #ያረጃል፤ ይወድቃል ጠንካራ ወጀብ በናጠው ቁጥር። አውሎን መቋቋም ሲሳነውም ይገረደሳል። እሳት ከጎበኜውማ ይፈልሳልም። ፍልሰቱ ለዘር ሳይበቃ ይሆናል።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአቅሙ ውስጥ ማሰብን፤ በአቅሙ ውስጥ መስከንን፤ በአቅሙ ልክ መመኜትን፤ በአቅሙ ልክ ማቀደን፤ በአቅሙ ልክ እራሱን ማደራጀትን፤ በአቅሙ ልክ እራሱን መምራትን ይለማመደው። አቅም ከኖረ አቅም ያለው ተጨማሪ #አቅም በራሱ ጊዜ ከች ይላል። አቅም #አጃቢ አይሻም፤ አቅም በፕሮቶኮል ከፍ እና ዝቅ #አይደናገጥም። ምኞትም ጥሎ አይበረግግም።
ማን ይሁን ማን? መታመን ካለበት፤ ማመንም ካለበት በውስጡ ባለው ሊያዘው፤ ሊያደራጀው፤ ሊመራው በሚችለው እራሱ በገነባው የአቅም አስፈፃሚ #ተቋም ብቻ ሊሆን ይገባል። ይህን ያደረጉ አገሮች፤ ማህበረሰቦች፤ በግል ህይወትም ቀውጢው የዓለም ሆነ የብሄራዊው ውጥንቅጥ ጦሮ ይሁን ኩነት፤ መልካም ጠረን ያለው ንቅናቄ ቢከሰት ሁሉንም በመረጋጋት የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል። ለዚህ በሰፊ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች ሆነ የኢኮኖሚ ፈላስፎች፤ የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪወች ዘንድ፦ እንዲሁም በሥነ ልቦና ሙሁራን፤ በሃይማኖት ሊቀ ሊቃውንታትም በአትኩሮት ሊጠና የሚገባው እንደ እኔ እንደ ሥርጉትሻ ዕይታ #የእምዬ #ሲዊዘርላንድን የጠሞነ ተግባር ነው።
በግል የህይወት ገጠመኝ እንኳን ምስጋና እንኳን #አታብዙብን፤ ስጦታውንም #በልክ የሚሉ፥ ልዕለ - ልዕቁ አገር ያላቸው የጨመቱ፤ በዴሞክሪያሳዊ መንፈስ ሰውኛ እና ተፈጥሮኛ አመክንዮች ሳይዘሉ ወይንም #ሳይተኙ፤ ወይንም ሳያዘግሙ ወይንም ሳይፈሉ ወይንም እንደ በረዶ #ሳይጋገሩ፦ ሳያፈሱ ወይንም ሳያፈሱ ሁሉንም የመኖር ስጦታወች በልኩ ለልኩ በራስ አቅም፤ በራስ ተመክሮ፤ በራስ ክህሎታዊ ተቋም እና በፈጣሪ አክብሮት እና ልዕልና በትህትናዊ #ህሊናዊነት ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለው የአመክንዮ አያያዝ ይዘት ሳስተውለው ሁልጊዜም ይገርመኛል። ሁልጊዜም ይደንቀኛ። በገጠመኞቼ ሁሉ በማያቸው ስክን ያሉ የተረጋጉ ክስተቶች ይማርከኛል።
እምዬ ሲዊዝ ለሚፈሉ እሳቢወች ቅጣት አላቸው ብዬ አስባለሁኝ። ለሰከኑትም ዕለታዊ የህይወት ኮርስ አላቸው። ቅጣቱም ሆነ ትምህርቱም ግን ነግረው፤ አውጀው፤ ተንጠራርተው በፍጹም አይደለም። እያንዳንዱ ነዋሪ እራሱ ያለበትን የሰብዕና አገነባብ በህሊናው ይዳኜው ዘንድ #ዕድል ይሰጣሉ። ለመማር ለፈቀድ። ሰው ሆኖ መፈጠሩን ላከበረ። ሲዊዝ ነዋሪ ሆኖ ስክነትን ያጣ፤ በጭካኔ የተመረዘ ሃሳብ ማራመድን፤ ወይንም በድብልቅልቁ ዓለም እዬዋኜ ለሌላው #ሰላም መነሳትን የሚሻ ሰብዕና ሲዊዝ አልኖረም ወይንም በዛች በምትናፍቅ በአት አልተፈጠረም ማለት ይሻለኛል።
እምዬ ሲዊዝ የአውሮፓ ህብረት አባል አገር አይደለችም። እምዬዋ #ወደብ የላትም። ነገር ግን በራሱ አቅም ላይ ያሰበ፤ በራሱ ችሎታ ላይ የተደራጄ፤ በራሱ ትልም ላይ ያተኮረ፤ በራሱ ህሊና በርጋታ የሚጓዝ የፖለቲካ ሥርዓት #በጽናት ገንብታለች። ስለዚህም በዓለም ዓቀፋ ወጀብ መሃልም ህዝቧን አስክኖ ለመታደግ ዕውቀቱ - ተመክሮው - ክህሎቱ #ለዊዝደም እንዳበቃት ይሰማኛል።
በፋክክሩ፤ በፍጥጫው፤ በከፍና ዝቁ፤ በፈንጠዝያው ውስጥ ኮሽ አይሏ እምዬ ሲዊዝሻ #የለችበትም። ዘውም የለም። ቁጥብ እና ጥንቁቅ ፖለቲካን ታራምዳለች፤ ለዛውም እዩኝ እዩኝ የሌለበት። እናም ያፈራ፤ ያሰበለ፤ በዬዕለቱ #የሰው #ግብር የማይቀርብበት፤ የእናቶች ማህጸን #ለቄራነት ፈጽሞ ያልታሰበበን የውድመት ማህበርተኛ የሆነ #ቀውስ የለባትም።
#ምሳሌ ላንሳ ከውስጤ ስለፀነስኩት ሰማዕት።
ወጣት ሳሙኤል አወቀ የሚባል ወጣት የህግ ባለሙያ ነበር። በዘመነ ሰማያዊ ህወሃት #ቅጥቅጥ አድርጎ ደብድቦ ገደለው። ሰማዕት ነው። ሰማዕቱ የህግ ባለሙያው ሳሙኤል አወቀ በወቅቱ ዕውነት ነው ብሎ ባመነበት ለሰማያዊ ፓርቲ ተልዕኮ እራሱን ሰጠ። ዛሬ እናቱን ጠያቂ ይኖር ይሆን? አላውቅም።
እራሱ ሰማያዊ ከሁለት ተከፍሎ፤ በዛም ሳይቀጥል እንደ ሰማዕቱ ክብር ልክ ሳይሆን በሰውኛ አኳኋን አለፈ። መሪው ኢንጂነር ይልቃል ኢኃን የሚል አዲስ ድርጅት ፈጠሩ። እሱን ጉልበተኛው የኢትዮጵያ ምርጭ ቦርድ ሰረዘባቸው። ከዛ ህብርን ተቀላቅለው ምርጫ ላይ ተሳተፋ - ተወዳዳሪ ሆኑ። እሱም አልተሳካም። ዛሬ ስደተኛ ናቸው። በፋኖ ጉዳይም ማዕከል እንደሆኑ ዓይነት ከቃለ ምልልሳቸው እረዳለሁኝ።
እንግዲህ ሰማያዊ ፓርቲን መሥራቹን አምኖ የተጠጋው ሰማዕቱ ሳሙኤል አወቀ መሬት ላይ አረጄ። ወጣትነቱ ተዘረፈ። ወድቀው ተነስተው ባትለው ያስተማሩት እናቱም ማቅ ለብሰው ዕድሜያቸውን ይገፋሉ። እስኪ ጠሩ። በዚህ በሰማዕቱ ሳሙኤል ተምሳሌት ሙሉ 60 ዓመት ስንት ትውልድ ባክኖ ቀረ? ስኬቱስ የት ደረሰ? ተቋማዊ አቅሙስ ምን ላይ ይገኛል? ዛሬም እንደ ትናንቱ የሰው ሰብዕና ጥገኛ የሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነገም በትርፍ አልቦሽ ግጥግጦች ቀጣይ ይሆናል?
ተቋም ቢኖር። እራሱን ችሎ የሚቆም የሃሳብ አቅም ቢኖር ስንታገለው ከነበረው ከህወሃት ሰራሽ ኦህድድ እና ብአዴን ሥር ድክ ድክ እያልን "የኢትዮጵያ ሱሴ ናት" ዕብለታዊ ግርግር እንታደም ነበርን? አቅማችን እና ህሊናችን በገፍ ለዛ እንገብር ነበር። ለክፋ ቀን ያስቀመጥነው አቅም እንኳን አልነበረነም። እራሳችን አሟጥጠን፤ በራችን ቧ አድርገን ከፍተን፤ ልባችን ፏ አድርገን ሰጥተን የሆነውን ሆን። ተዘርዝሮ ለማያልቅ ተመን አልቦሽ ስጋት፤ ፍርሃት፤ ቀውስ፦ ህልፈት፤ ንቅለት፤ ሰኔል ተዳረግን። የተሰደደውም ፊት ለፊት የጋመው ባያገኜን ወላፈኑ አጋይቶናል። ሰላማችን አጥተናል። ባክነናል። ከራሳችን ቤተሰቦች ጋርም በፖለቲካ አቋም እንደ ተለመደው ተለያይተናል። ለምን? እራሱን የቻለ የሃሳብ አቅም ስሌለን። ሁልጊዜ ጥገኛ።
ሁልጊዜ በአዳዲስ ኢቤንት ምርኮኝነት? እስከመቼ? አቅም ያለው ሰብዕና ስኬቱ ትውልድን ማዳን ነው። ታሪክን ቅርስን ድልን ትውፊትን አደፍርሶ ወይንም አጎፍሮ ሳይሆን አክብሮ የተገኜ በእኔ ዘመን አላዬሁም። የነባር ሥም በአዲስ ቅጥል ሥያሜ ስኬት አይሆንም። አዲሱ ትውልድ ያልተብረቀረቀ፤ የሚያዳልጥ፤ ሻሞ ያልበዛበት፥ የውዳሴ ከንቱ ግጥግጥ የማይፏልልበት፤ የሰከነ የራስ እንደራሴ የሚያደርግ የአስተሳሰብ ቅኝት ሊኖረው ይገባል።
የ60ወቹ የፖለቲካ ዋናተኞችን የፖለቲካ ግርፍን ተከትሎ ያለው ጉዳይ በሰብዕና ላይ መጠለል "ዙሮ ዙሮ ወቅን" ይላሉ በጎንደር ገራገሮቹ የወገራ ነዋሪወች። ወቅን ለወገራ አውርጃ ከተማ በቅርብ የሚገኝ ተራራ ነው። በዬትኛውም አቅጣጫ ወደ ገበሬ መንደሮች ብትዘልቁ ወቅን ከላይ ቁብ ብሎ ያያችኋል። እናም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙሮ ተዟዙሮ ከከሰለ፦ ከተቃጠለ የካርቦን ዕሳቤ ሆነ ሰብዕና ተስፋን ማቀድ አድካሚ ነው።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሆይ! ራሱን የቻለ ሃሳብ አፍልቁ፤ ተቋም ፍጠሩ በተቋሙ መስራች ሰብዕና ሳይሆን በተቋማችሁ የአቅም ማንነት ላይ ተጠለሉ። ጎዳናችሁ ይህ ይሆን ዘንድ ምኞቴ ነው። ከሁሉ በከንቱ ከዚህም ከዛም እዬተቦጫጨቀ ባክኖ የሚቀረውን የአቅም ፍሰታችሁን ቆጥቡ። ክህሎታችሁን ለማይቀልቅ ቅጽበታዊ ዕሳቤ አትባክኑት፤ አታባትሉት። መፈጠራችሁን አክብሩና በጥንቃቄ አስቀጥሉት። መኖራችሁ መማር የሚችለው ሆነ የነፃነት ራህባችሁን የሚያጠግበው መኖር ስትችሉ ነው። ከዛገ ዕሳቤ፤ ከማረተ ጉዳይ ተስፋችሁ በተሃድሶ ሊከብር ፈጽሞ አይችልም። ነገን ለማሳቅ የሃሳብ አቅም ራስን በመቻል ቀምሩ።
ዛሬም ሺወቹ ካቴና ላይ ይገኛሉ። ዛሬም የታገ ቱወገኖች አሉን። ዛሬም ሰላሙን አጥቶ በሚከፍለው ግብር በሚገዛ ድሮን የሚጨፈጨፍ ወገን አለን። ዛሬም ከፍርሃት ጋር የተጋቡ ሚሊዮን ዜጎች አሉን። ዛሬም የተሰወሩ ቤተሰቦች አሉን። ዛሬም በየሰከንዱ ጭንቀት ስንቃቸው የሆነ ሰላም የራባቸው አካሎች አሉን፤ ዛሬም ጠኔ እያገላበጠ የሚገርፋቸው እኛወች አሉን። እኛ ደግሞ የሥም መዘክር፦ የፎቶ ፋክክር የውዳሴ አታሞ፦ ቁምነገር ሆኖ በዛ ፋክክር ላይ ከፍ ዝቅ እንላለን።
ትውልድ የሚድነው፤ አገር የሚተርፈው ከራስ ያለፈ፤ ከኢጎ የዘለለ ለእኛዊነት ሰባዕዊነት የሰገደ ሰብዕና ሲኖር ነው። ይህ ሰብዕና ተቋም ቢሆን ይዘልቃል። ያዘልቃል። ትውልድም የትውልድም ይሆናል። ተቋም የጠራ፤ የጠሞነ ተቋም ጥግም መሪም እንዲሆን ዕድል ይሰጠው። ቅንነት ማኒፌስቶ ይሁን። ለቀደመ የእኛነታችን ቋሚ ቅርስ ውርስም ቀናዕይ እንሁን። የጹህፌ ጭብጥ ይህ ነው።
#ክወና።
በምንተቸው፤ በምናብጠለጥለው፤ በምንወቃቅጠው ክስተት ሁሉ በዕውን እኛ አለመኖራችን እናረጋግጥ። ለታረመ አንደበት እራሳችን እንግራ። አክሰሱ ላላቸው ልጆቻችን ይጭነቀን።
ቸር አስበን፦ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን። እሾህ አሜኬላ ውዶቼን አይንካብኝ። አሜን።
እግዚመብሄር ይስጥልኝ። አሜን
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergugut©Selassie
22/01/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ