#ጨርሶ - #መጨረስ #መጫረስም #ዛሬን #ያደርቀዋል- ነገን ያጨሰዋል።

 

"አቤቱ አንተ አምላኬ ነህ፤ ድንቅን
ነገር የዱሮ ምክርን በታማኝነትና
በዕውነት አድርገኃልና ከፍ ከፍ
አደርግኃለሁ ስምህንም አመሰግናለሁ።"
(ትንቢተ ኢሳያስ፤ ምዕራፍ ፳፭ ከቁጥር ፩ - ፪)
 
(ምዕራፍ ፳።)
 
ክብሮቼ ማህበረ ሥርጉትሻ ቅኖቹ የውስጦቹ እንዴት አደራችሁልኝ?
እንደምን አረፈዳችሁልኝ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ እናንተን ይዤ
ምንም አልሆንም። ትህትናችሁ፤ ሙግታችሁ፤ ቅንነታችሁ ቁሞ
አዘውትሮ ያስተምረኛል። ለእኔ ዩንቨርስቴወቼ ናችሁ። ኑሩልኝ። አሜን።
 
#በር እንደ መግቢያ።
 
ዕድሜ ስክነትን፤ ዕድሜ እርጋታን፤ ዕድሜ ጭምትነትን ካልሰጠ እኔነት ይሰወራል ወይንም ይሸሻል።
ወጣቶች ዕድሜያቸው የሚያስገድዳቸው ሁነቶች አሉ። ተሎ ተስፋ መቁረጥ፤ መበሳጨት፤ ትዕግስት
ማጣት፤ መቸኮል፤ መጣደፍ፤ መጓጓት፤ መቆጣት ረጃጅም የሆኑ የኩርፊያ አስፓልቶችን መዘረጋጋት።
ይህን አታድርጉ፤ እንዲህም አትሁኑ ወጣቶችን ለማለት አይቻልም። ትክክልም ነው ብዬ አላምንም።
 
ምክንያቱም እኛም አልፈንበታልና። ግን ነገር ግን የተሻለውን መንገድ የማሳየት ግዴታ ከታላላቆቻቸው
ይጠበቃል። ወጣቶችን አግልሎ፤ ከውስጥም አርቆ፤ ደንበር ይሁን ወሰን ሠርቶ ሳይሆን እንደ እራሳችን
የአብራክ ይሁን የመሃጸን ፍሬ አድርጎ መቀበል ቀዳሚው ተግባር ከታላላቆች የሚጠበቅ ይመስለኛል።
 
#ከውስጤ ለውስጤ።
 
ጨርሶ የውስጥን ብስጭት የግዴታ መስመር መከተል፤
በባሩድ ብቻ ሳይሆን በአሽሙር ይሁን ይፋዊ ግሳጼ ሰብዕናን ያለገደብ መዳፈር፤
ለዛሬም ለነገም ሳያስቀሩ መደፋፈር ይሁን እላፊ መሄድ፤
አጋጣሚው ሲገኝም ለዘር ሳያስቀሩ ሙልጭ አድርጎ የክፋ ሃሳብን ዓላማ ማሳካት፤
የተገባ አይደለም። በተለይ ሙሉ ዕድሜ ላይ ለምንገኜው ትውልዳዊ አደራም፤ ይሁን ኃላፊነትም አለብን። ኢትዮጵያ ጉዳዬ ናት፤ ኢትዮጵያ አጀንዳዬ ናት የምንል ከሆነ እራስን አሸንፎ መነሳት ይጠይቃል።
 
ገረጭራጫነት፤ ብስጭት፤ አግላይነት፤ ተጫኝነት በሙሉ ዕድሜ ላይ ላለ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጠቃሚ መርሆ አይደለም። ኃላፊነት ከወንበር ጋር፤ ከሹም ሽረት ጋር፤ ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እና አካልነት ጋር ብቻ ሊታይ አይገባም።
የዚህ ትውልድ ቤተኞች፤ የዚህ ትውልድ ዘመንተኞች ነን እና ኃላፊነት ደረጃው ቢለያይም፤ አፈፃጸሙ ቢለያይም ሁሉም ኃላፊነት አለበት ለኃላፊነት። ተጠያቂነትም እንደዛው ነው።
 
#የሰከኑ ወጣቶች።
 
እንደ ዕድል የሰከኑ፤ የተረጋጉ ወጣቶች ይኖራሉ። ከድምፃቸው፤ ከአነጋገር ዘያቸው፤ ከአቀራረብ ይዘታቸው ጀምሮ የሰከኑ ወጣቶች ይገጥማሉ። ታላላቆች ከእነሱ ልንማር ብንፈቅድም መልካም ይመስለኛል። ትምህር ከተፈቀደለት ከንፋስ ንቅናቄ እንኳን ብዙ መማር ይቻላልና። የሚበልጡን ጭምት ወጣቶች አሉ። ለእነሱዕውቅና መስጠቱ አትራፊ መንገድ ይመስለኛል።
 
አየሩ ብስጩ ነው። አየሩ ያረገርጋል። በቀል እንደ ጀግንነት የሚታይበት ጊዜ ላይ ነን። መጫን የመፍትሄ ቁልፍ ሆኖ የሚታይበት ወቅት ላይ ነን። ይህ በእኛ ብቻ ሳይሆን ሰፋ አድርገን ሉላዊውን ስናማትር ያልኩትን ግብረ ምላሽ ታዩታላችሁ።
 
#አድማጭነት። በድርበቡ ጥቂት ጉዳዮች ላነሳ ……
 
አድማጭነት ኢኒስቲቲዊት ነው። ማድመጥ ጥበብም ነው። ማድመጥ ክህሎትም ነው። ማድመጥ ከንግግር ጥበብ ውስጥ አንዱ ዓውራው ክፍለ አካል ነው። አንድ ሰው ርቱዑ ባይሆን ቢያንስ የማድመጥ አቅሙ ላይ ሊሰራ ይገባል። አድማጭነት በተፈጥሯችን ለሁላችም እኩል የተሰጠን ጸጋ ነው። የጆሮ ሚና፤ የህሊና ድርሻ፤ የዕዝነ ልቦና አፈጣጠር ለመኖራችን ሁሉ የማድመጥ አካልነት የተፈጠሩ ናቸው።
 
በማድመጥ ውስጥ ዕውቀት፤
በማድመጥ ውስጥ መደመጥ፤
በማድመጥ ውስጥ ሃሳብን የማደራጀት አቅም፤
በማድመጥ ውስጥ ማስተዋል፤
በማድመጥ ውስጥ ፍልስፍና፤
በማድመጥ ውስጥ ስክነት፤
በማድመጥ ውስጥ መዳን እና ማዳን፤
በማድመጥ ውስጥ ማከም እና መታከም፤
በማድመጥ ውስጥ ሰላም እና ጸጥታ፤
በማድመጥ ውስጥ ፍትህ እና ዳኝነት፤
በማድመጥ ውስጥ ብቁ ሰብዕና ወዘተ መገንባት ይቻልበታል።
የማድመጥ አቅምን መፈተሽ፤ የማድመጥ አቅምን መመርመር ከራስ ለራስ መፍቀድ ይገባል።
 
#እላፊ መሄድ አይገባም።
 
"ህግ ተላላፊወችን ጠላሁ" ይላል ልብአምላክ ዳዊት። ለሰማዩም ለምድሩም ሂደት እግዚአብሄር የፈጠረውን የሰው ልጅ አክብሮ መነሳት ይገባል። #ቅጥልጥል አያስፈልግም። "መንጋ፤ ጃዊሳ፤ ጅራሬ፤ የቀነጨረ" ሌሎችም አሉ። አይገባም። ፈጣሪን መዳፈር ይሆናል። ፈጣሪ ሲፈጥረን እናመሰግነው ዘንድ እንጂ #አሻቅበን በሥልጣነ መንበሩ ላይ ልንዳፈረው አይደለም።
 
ዜና ላይ እስኪ እዩት አሰቃቂ የተፈጥሮ አደጋ በመላ ዓለም አለ። ሥልጣኔን - ሥልጣኔ እንዲያጠፋ ሲፈቀድለትም የሰው ልጅ ሰቆቃ በሁሉም ቦታ አለ። #እረፍት የለም። 
 
ቢያንስ እኛ በተለይ ሙሉ ዕድሜ ላይ የምንገኝ በእጃችን በሚገኝ ነገር አምላካችን፤ አላኃችን እንዳይከፋ፤ ምርቃት ተነስቶ፤ እርግማን አና እንዳያይል ከእያንዳዳችን በግል ከሁላችንም በጋራ እራስን የመግራት ኃላፊነት አለብን። እኛ የራሳችን እንደራሴወች ነን እና። በተለይ አክሰሱ ላላቸው ታዳጊ ወጣቶች እክል ላለመሆን እራስን ማሸነፍ፤ እራስን መግራት፤ እራስን መቆንጠጥ በእጅጉ ያስፈልገናል።
በቅርቡ ከአንዲት ትጉህ ወጣት ጋር ስፃፃፍ "ጸልይልኝ" አልኳት። "እሺ አለችኝ እና #ለሁሉም ነው እኔ እምጸልየው" አለችኝ። ምን ብለሽ ስል ጠየኳት "ለሁሉም #ልብ ስጥ ብዬ" አለችኝ። ያቺ ብልህ ኃላፊነት የሚሰማት ትንሽዬ ወጣት እንዳለችው ለሁላችንም አምላካችን፤ አላኃችን ልብ ይስጠን። አሜን። 
 
ከወጀቡ - ከወጮፎው - ከረግረጉ - ከጨቀጨቁ - ከጦሮው ከተጋራፊው - ከተዳፋሪው ክፋ መንፈስ እግዚአብሄር ይጠብቀን። አሜን። በፍጹም በፍጹም #ክፋነት #ሊናፍቀን አይገባም። መዳኛችን አይደለምና።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
01/10/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
"#እናስተውል።"
See less

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።