#ማሸነፍ #በሃሳብ #ልቅና #በድርጊት #ልዕልና።

 

"ዳግመኛ አርበኞች ቢከቡኝ እኔ በሱ አመንሁ
እግዚአብሄርን አንዲት ነገር ለመንሁት ያቺኑ
እፈልጋለሁ ብሎ እንደ ተናገረ በሱ ያመኑ
ሰወች ፍራት የለባቸውም በሱ ያመነ ሰው
ለዘላለሙ በሕይወት ይኖራል ከክፋ ነገርም
የተነሣ አይፈራም" (መቃብያ ፯ ቁጥር ፫)
 
 
አዱኛወቼ ቤተ - ሥርጉትሻ እንዴት ነን?
ጤና ይስጥልኝ ኢትዮጵያ እንዴት አድረሽ - አረፈድሽ ይሆን?
 
#ዕፍታ ላፍታ።
 
ማሸነፍ ደስታ ይሰጣል። መሸነፍ ደግሞ ውስጥን ያጠነዝላል። ለብልህ ሰው ግን መሸነፍን የመቀበል አቅም ከኖረው ውስጡ ሳይጠነዝል ወይንም ሳይጠወልግ ለቀጣይ የህይወት መስመር ሁሉ ከእግዚአብሄር ነውና አቅሙን አበረታቶ፤ ከአቅሙ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ መክሮ እንደ ገና አወን እንደገና የመነሳት ዕድል ሊኖር ይችላል።
 
#ማሸነፍ። የሚያሸንፈው ጥራት ያለው ሃሳብ እና ድርጊቱ ነው።
#መሸነፍ። የሚሸነፈው እና የሚወድቀው ሃሳቡ እና አካሄዱ ነው።
#መሸናነፍ። ቅይጥ ነው ይሄ የኪሳራ እና የትርፍ ምንዛሬ። የታክቲክ እና የስትራቴጂ ክህሎትም።
 
በጦር ሜድ ብቻ አይደለም የለቱ የወግ ገበታዬ ሊያጋራችሁ ያሰበው። በማህበራዊ፤ በጥበባዊ፤ በሃይማኖታዊ፤ በፖለቲካ፤ በኢኮኖሚያዊ፤ በትዳራዊ ወዘተ ገጠመኞች ውስጥ ሰው በሁለት ቢከፍለውም የእኔ ፈንገጥ ያለው ዕይታ #መሸናነፍ የሚል አክዬ ወደ ሦስት ከፍ አድርጌዋለሁኝ። ተጋጣሚው ድህነት ቢሆን ብላችሁ እሰቡት ወይንም ጤና ማጣት ቢሆንስ ብላችሁ ዕድል ስጡት፤ ወይንም ትምህርታዊ ጉዳይስ ቢሆን ብላችሁም ማስላት ትችላላቸው። መኖር እና ጅረቱ ወዘተረፈ ነውና። 
 
#ተዚህ ላይ ፈንገጥ ያሉ ዕይታወቼን ብደጋግማቸው መልካም ነው።
 
1) ልክ ከዚህ ቀደም እንደገለጽኩት ጨለማ እና ብርኃን ብቻ ሳይሆን #ግራጫም ሦስተኛ አለ። ሊመሻሽ ሲል፤ ሊነጋጋ ሲል የሚል ጽኑ ዕምነት አለኝ። ግራጫማ ገጠመኜ የህይወታችን ክፍለ አካል ነው ብዬ አምናለሁኝ።
 
2) በሼኪስፔር ፍልስፍናም ኮሜዲ እና ትራጀዲ የሚለው፤ ለእኔ ተውኔት ይሁን ተጨባጭ የሕይወት ምግባር በሦስት ሊታይ ይገባል ብዬ አምናለሁኝ። ከኮመዲ እና ከትራጀዲ ባልተለዬ ሁለቱንም ቀይጦ የሚገኜው በኢትዮጵያ #ሲቃ የሚባል ሳቅ እና ዕንባ የተቀላቀለበት ትዕይንት አለ ----- እና። አንዲት እናት በብዙ ድካም ልጇን ብቻዋን አሳድጋ የክብር ማዕረገኛ ሲሆን ሳቋም ለቅሷም በውህደት ይገለጣሉ። ያንጊዜ የተንጠራራ ደስታን ትንሽ ጫን የሚል የዕንባ ጠብታወች ይኖራሉ፤ ዕንባው ሲፈስ ግን ቁስለትን ሳይሆን እርካታን ያመጣጥናል።
 
3) ሰብዕና። በሰብዕና ዘርፍም ብርኃናማ ጨለማ የሆነ ዕሳቤ የሚያራምዱ ይኖራሉ። ክፋ ሃሳብ የወጣለት አጥማጅ ነውና። የሆነ ሆኖ የሁለቱ ቅይጥ ደግሞ ወይ ጨለማዊ ወይንም ብርኃናዊ የማይባል፤ በዝንቅንቅ ስሜት ወይንም ፍላጎት ሊመደቡ የሚችሉ ሰብዕናወች ይኖራሉ። ለዚህ #ግራጫማ - በሲቃ የሚል ሰብዕና እሰጠዋለሁኝ። ከ10 ዓመት በፊት ጽፌበታለሁኝ። 
 
በቅጽበት ስሜታቸው ለሚቀያየሩ ሰብዕናወችን ሳይ በተመሳሳይ ደቂቃ ሳቁን አቅርበው ጎንጨት አድርገን ሳይጣጣም #ማት ያወርዳሉ፤ የማቱን ጫና ሳንቋቋም ደግሞ ውሽክ በሉ ይሉናል። ይህን ሰብዕና ዝንቅንቅ ስለሆነ ብይን ለመስጠት ያዳግታል። #አሳቻ ወይንም #ቅጽበታውያን የሚለው ቃል ሊገልጸው ይችላል።
 
4) ደስታ እና ሐሤት። በደስታ እና በሐሤት መካከልም እኔ ሁለቱን ለይቼ ነው እማያቸው። ሐሤት የመጨረሻው በእግዚአብሄር የተመረቀ የሥጦታ ዘመን ነው ብዬ አምናለሁኝ። ደስታ ለገኃዱ ዓለም ብቻ አገልጋይ እንደሆነ አስባለሁኝ።
 
5) ፍትህ እና ርትህ። ፍትህ ከሚዛን ጉዳይ ጋር ብቻ ሳይሆን የህሊና ሥልጣኔም ነው ብዬ አምናለሁ። ቢሆንም ግን ፍትህን ርትህን እንደሚበልጠው አምናለሁኝ። ከእግዚአብሄር የሆነ የዳኝነት ብይን #ርትህ ነው ብዬ አስባለሁኝ። 
 
6) የንግግር ጥበብ። የንግግር ጥበብን መምህሬ ጋሼ አብነት ሲያስተምረኝ ሁለት ዓውራ ቤተኞች እንዳሉት ነበር። ተናጋሪ እና አድማጭ ብሎ። እኔ ደግሞ በመኖር ውስጥ፤ በመድረክ መሪነት እና አደራጅነት ሥሰራ በነበረበት ጊዜ ከሁለቱ ያልተለዬ አቅም ያለው ሆኖ ያገኜሁት የአድማጩን እና የተናጋሪው ችሎት #ግብረ - መልስ (ፊድባክ) እንደሆነ ወስኛለሁ። ስለሆነም ንግግር ሁለት ብቻ ሳይሆን ሦስት አካላት እና በርከትከት ያሉ ጅረቶች እንዳሉት አስባለሁኝ።
 
7) ዛሬ ደግሞ ማሸነፍ፤ መሸነፍ እና መሸናነፍ ሦስቱም እኩል አቅም አላቸው ብዬ አስቤ መጣሁኝ። ይህ ገጠመኝ ጊዜም ሊያስገድደው፤ ሊገዛውም የሚችል ይመስለኛል። የሆነ ሆኖ ፈንገጥ ያለ ዕይታ በእኔ ቤት የተለመደ ነው እንደማለት።
 
#አንድ ሰው እና መኖሩ።
 
ተቋማዊ ሁነቶችን ቆዬኝ ብዬ በአንድ ሰብ የአኗኗር ዘይቤ ላተኩር ወደድኩኝ። አንድ ሰውም መኖሩን የሚመራው ከሃሳብ ነው የሚነሳው። ሃሳባቸው የተደራጄ ሰብዕናወች በወጀብ መሃልም መኖራቸውን የሚያስቀጥል የድርጊት ሁነኛ ዘብ ይኖራቸዋል። ለምን ኤክሲሞ አይሆንም። ለምን ጭልጥ ያለ በርኃ አይሆንም። 
 
በሃሳብ ብቃት ብርታት - ጥንካሬ - ዘመንንን የማድመጥ - የመቀበል - ዕውቅና የመስጠት አቅም ከሃሳብ ልቅና ወይንም ጥራት ይነሳል። አንዲት የእኔ ቢጤ እናት በጉልበት ከሌላ ተቀጥራ፤ እንጀራ እየጋገረች፤ ልብስ እያጠበች አሳድጋ ቁልፍ የአገር መሪ ልጅ ሊኖራት ይችላል። ለምን? መኖርን ያስተናገደችበት የሃሳብ ልቅና በድርጊት ልዕልና ስለከበረ።
 
ረህብ ፈተናዋ ነው ለዚህች ሴት። ረሃብ እንዳያሸንፋት ድህነቷን መቀበሏ ዋና የስትራቴጂዋ ምኽዋር ነው። ከድህነቷ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ወዘተረፈ ፈተናወች ጋር እሷ ላለመሸነፍ፤ እነሱ ለማሸነፍ ሲፋለሟት መሸናነፋን በድል የምታበስረው መኖሯን ማስቀጠል ችላ መሽቶ ሲነጋ እሷ ሳትሰበር በጥንካሬ ጎዳና መገስገሷ ነው። ሴቶችን የሚፈትን ፆታዊ ጉዳይም አለ። 
 
ለዛች የእኔ ቢጤ ባተሌ ችግሩ አለ። ድህነቱ አለ። መጠለያም የረባ ላይኖራት ይችላል። እራፊም ለእሷም ለልጇ ላይኖር ይችላል። እሷ ግን እየዞረች በየቤቱ እንጀራ፤ አብሽሎ ትጋግራለች፤ ልብስ ታጥባለች፤ ወይንም ጠላ ጠምቃ፤ አረቂ አውጥታ እየሸጠች ልጇ ይማራል። ልጇን ካሰበችው አድርሳ መንጋቱን ስታይ አሸናፊዋ እሷው ትሆናለች። ይህ በኢትዮጵያ ከገጠር እስከ ከተማ የኢትዮጵያ ሴቶች በፈተና ወድቀው ሳይቀሩ ልጆቻቸውን ለቁምነገር ያበቁ የአብዛኞቹ እናቶች #ገድል ነው።
 
ትዳር ሲፈርስ መሸነፍ ነው። ትዳሩ የተመሠረተበት ሃሳብ ልል ስለሆነ ይሆናል። ፍቺን መቀበል በብዙ ይፈትናል። በጎስቋላውም ትዳር ደስታ ሰጪ ጉዳዮች ሊኖሩ ስለሚችሉ። እራሱ ባለትዳር መባል በእኛ ማህበረሰብ የክብር ዘውድ ነው። ፈትነት ደግሞ??? ልጅ ማግኜት በራሱ ሐሤት ነው። ከደስታ በላይ። አንዲት ሴት ማርገዝን፤ መውለድን እናት መባልን ማግኜቷ ከተፈጠረችበት ሚስጢር ጋር መኖር ማለት ነው። እናትነት ክህሎቱ #እዮራዊ ነውና።
 
በጋብቻም ይሁን ከጋብቻ ውጪ ለተወለዱ ልጆች፤ ወደ ቀደመው ስመለስ ሰፊው ኃላፊነት ከእናቶች ላይ ወይን ከእናታቸው እናት ላይ ይወድቃል። ግን እናቶች በላቀ የሃሳብ ጥራት ፈተናን ገርተው መሸነፋቸውን ተቀብለው፤ ግን የተሸነፋበትን መስመር አርመው ከጥገኝነት ወጥተው በጥረታቸው የልጆቻቸውን ዕድል የሚድሩ፤ የሚኩል ጀግና የኢትዮጵያ እናቶች #ካሪክለም ናቸው። 
 
ብዙውን ለቁም ነገር የበቁ ታዋቂ ሰወች፤ ተጽዕኖ ፈጣሪወች በአንድ ክንድ ያደጉ ናቸው። ባይበዛም በፈተና ውስጥ አልፈው እራሳቸውን በዲስፕሊን ገዝተው ልጆቻቸውን ለወግ ለማዕረግ እስከ ዓለም ዓቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ያደረሱ አባቶችም ይኖራሉ። ቁምነገሩ በሞትም ይሁን በህጋዊ ፍች፤ በገጠመኝም ከጋብቻ ውጬ የተወለዱ ልጆች ዕጣ ፈንታቸው እንዳይስተጓጎል አሳዳጊወቻቸው ሁለገቡን ፈተና ተቋቁመው ለድል የሚበቁት የዓላማቸው የሃሳብ ጥራት ሲሆን ግበኛ የሚያደርጋቸው ደግሞ የድርጊት #ቱላቸው ይሆናል። ለዚህ ነው ዕርዕሴን ማሸነፍ በሃሳብ ልቅና፤ በድርጊት ልዕልና ያልኩት። 
 
በነገራችን ላይ ከእናት ወይንም ከአባት ውጪም በማር ልጅነት፤ በታላቅ እህት ወይንም ወንድም ወይንም በሁለቱም፤ ባለፈም በአጎት አክስት ዕድሉ ሊሳካ ይችላልም። ተረካቢው የእኔ ብሎ በጠራ ሃሳብ ድርጊትን ሰንቅ የመጓዝ አቅም ነው የግቡ መቋጫን ከሲቃ ጋር ሊያገናኘው የሚችል። 
 
#በዚህ ውስጥ።
 
ማሸነፍን ማንጠራራት ተገቢ አይደለም።
መሸነፍንም ማስቆዘም አይገባም።
መሸናነፍን ፈርቶ ዳር ቆሞ ፈተና ሆይ! ውቃኝም አይገባም።
 
በመኖር የጊዜ ሩም ውስጥ ሁሉንም ገጠመኝ በአደብ አቅርቦ መመርመር ይገባል። የሃሳብ አሸናፊነትን ለማብቀል መትጋትም አንኳሩ ጉዳይ ነው። ሌላው የአቅም ስርጭት እና ክፍፍል ጉዳይ ነው። #ለጠራ ኃሳብ ብቻ አቅምን ቆጥቦ ማስተዳደር ይገባል።
 
ህይወት ሁልጊዜም አማራጭ አለው። አማራጩ ግን እንደዬጉዳዩ ፈታኝ ሊሆን ይችላል። አቅምን መጥኖ በልክ መወሰን ይገባል። ሌላው ሁልጊዜ በተመሳሳይ ግድፈት መውደቅ፤ መሸነፍ ከኖረ ጠቅላላ የስትራቴጅ እና የታክቲክ ለውጥ በስርነቀል ሁኔታ ሊኖር ይገባል። ይህ ለግል ህይወትም ይሁን ለተቋማዊ ህይወት ወሳኝ ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁኝ።
 
#ጆሮ ከዕዝነ - ህሊና።
 
ጆሮ ያለው ሁሉ አድማጭ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ህሊና ያለው ሁሉም ማስተዋል ተሰጥቶት ግን አቅም ሊያንሰው ይችላል። ስሜታዊነት የሚፈትነው ሰብዕና ከህሊናው ጋር ከመምከር ስሜቱን ማቆላመጥ ሊመርጥ ይችላል። ልበ ብርኃን የሚባሉ ሰብዕናወች ይህ ሥያሜ ስለምን በማህበረሰባችን ተሰጣቸው ብለን እንሰበው። 
 
// የሆነ ሆኖ ማሸነፍ አድማጭነትን ይጠይቃል።
/// መሸነፍም አድማጭነትን ይጠይቃል።
//// መሸናነፍም አድማጭነትን ይሻል። ሦስቱም የተፈጠረውን ገጠመኝ በቅጡ ማድመጥን ይሻሉ። ሐኪሞች እኮ ወደ ላብራቶሪ፤ ወይንም ወደ ቀጣይ ምርመራ ለመላክ የሚያደርጉት ጥረት ከመጀመራቸው በፊት በሽተኛውን #ይጠይቃሉ ከውስጣቸው ያደምጣሉ። ሙሉ ሰውነቱን ያያሉ። በመሳሪያ አተነፋፈሱን ያደምጣሉ። 
 
አሸንፈህም ማሸነፍህን **** ልታደምጠው ይገባል።
ተሸንፈህም **** መሸነፍህን ልታደምጠው ይገባል።
ተሸናንፈህም አንተም የተወሰነ ነገር አግኝተህ፤ አሸናፊህም ብዙ እጁን ወስዶብህ ለምን ብዙ እጁ እንደተወሰደብህ ልታደምጠው ይገባል። 
 
እኔ ብልህ እናት ነበረችኝ። ሁለተኛ ከክፍል ስወጣ በአንድ ክፍል ተመራችሁ እንዴት ሌላው ተማሪ ከአንቺ በልጦ አንደኛ ሊወጣ ቻለ ብላ ታፋጠኝ ነበር። ለበለጠሽ በሌላ ክፍል የተማረው የለም ለምን አንቺ ሁለተኛ እሱ አንደኛ ወጣ ብላ አዲስ አጀንዳ ትሰጠኛለች። ጥረቴን አድምጬ እንድበልጥ መንገድ ታሳየኝ ነበር። ጠንክሬ እንድወጣ የጠራ የአጠናን ስልት እንድቀይስ ምህንድስና ታስተምረኝ ነበር።
 
እናቴ እብዬ ሆዴ ከእኔ በታች 40 ተማሪወች ሊኖሩ መቻላቸው አጀንዳዋ አልነበረም። ስለእነሱ ሳይሆን ስለበለጠኝ ተማሪ ሁኔታውን እንዳደምጥ ጥንካሬውን እና ድክመቱን አርቄ ሳይሆን አቅርቤ፤ የተሻለ ሃሳብ አፍልቄ፤ ሃሳቡን አቅጄ፤ ለተፈፃሚነቱ እተጋ ዘንድ ጠንክሬ እንድሰራ #ብርኃኔ ትሆን ነበር። በዚህው እንከውነው። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን። ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
03/10/026.
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
See less

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።