ኢትዮጵያዊነት የሳሙና #አረፋ ፕሮጀክት አይደለም።

 

ኢትዮጵያዊነት የሳሙና #አረፋ ፕሮጀክት አይደለም።
 
"ዳዊት በእግዚአብሄር አመንኩ፤ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል
ብዬ ብሎ እንደ ተናገረ በእግዚአብሄር ባመኑ ሰወች ግን ፍርሃትና
ድንጋፄም የለባቸውም።" (መጽሐፈ መቃብያን ምዕራፍ ፯ ቁጥር ፩።)
 
 
የእኔ ክብረቶች እንዴት አደራችሁ? አረፈዳችሁ? ዋላችሁልኝ?
ፈላስፊት ኢትዮጵያስ በአያሌው እንደምን አለሽልኝ? ከቶ አዳርሽ እንደምን ሆኖ ይሆን? #አይዞሽ እናቱ።
ስለ ኢትዮጵያዊነት እኔ ስጽፍ በመኖር ውስጥ ሆኜ ፈትኜ ያገኜሁትን ቁም ነገር ነው የማጋራችሁ።
ኢትዮጵያዊነትን ከፖለቲከኞች አንፃር ሰፍሬው አላውቅም። 
 
ኢትዮጵያዊነት ከፖለቲከኞች በፊት የቀደመ ስለሆነ፤ ከእነሱ ጋር ማፎካከር የኢትዮጵያዊነት ደረጃ ይፈቅደዋል
የሚል ዕምነት የለኝም። ኢትዮጵያዊነት ከኦርጋኒክ የተገኜ፤ አርቲፊሻል ወይንም ፌክ ያልሆነ ስለመሆኑ መኖሬ
አስተምሮኛል እና። 
 
ስለሆነም የእኔን የልብ ትርታ፤ መንፈሴን ስገልጽ የኢትዮጵያዊነት የሥልጣኔ ክህሎት ለውስጤ ብርኃን አመንጭነቱን
ደርሶኝ የምመገበው የመንፈስ የማይነጥፍ #ጥሪቴ ስለሆነም ነው። ከእቅፋ ፈቅ ብዬ አላውቅም። ስለሆነም ማህባው፤
ጸዳሉ፤ ማዕረጉ ይሁን ሞገሱ ተነጥሎኝ አያውቅም።
 
በመዋለ ዕድሜዬ በኢትዮጵያዊነት ላይ በሚያላግጡ፤ በሚያቃልሉ፤ ቅናት ድብን አድርጎ እንደ እህል በሚወቃቸው፤
የሚቁነጠነጥ መንፈስ በሚኖራቸው ፤ የሚረገርግ ስሜት ያላቸውን ነፍሶች አላዳምጥም። በሽታ በጊዜየ ለመግዛት
ፈቃደኛ አይደለሁም እና። ቁርጡን ስነግራቸው ኢትዮጵያዊነ መንፈሱ #የማይደረስበት ማንነት ስለመሆኑ ማህተም አለበት።
 
"አድርገህልኛል እና አመሰግንኃለሁኝ።" 
 
የጸና - የተረጋጋ - የመኖሬ መክሊት እንብርቱ፤ ህሊናው ኢትዮጵያዊነት + ኢትዮጵያዊነት + ኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮጵያዊነቴን
እወደዋለሁ። ኢትዮጵያዊነቴን አከብረዋለሁኝ። ኢትዮጵያዊነቴን #አመሰግነዋለሁም። የአሰተሳሰብ ድህነት፤ የሃሳብ መጫጫት
የጭካኔ ስርክራኪ እንዳይገጥመኝ ያደረገው ብቸኛው ዩንቨርስቲዬ ኢትዮጵያዊነት ነው። 
 
ለዚህም "መሬትን ተጠንቅቀሽ እርገጫት" እያሉ ላሳደጉኝ አባቴ አቨይ እና እናቴ እብዬ፤ መላ ቤተሰብ(አክስት አጎት፤ ጎረቤት፤) መምህራን የጎንደርን ህዝብ በሙሉ፤ በሥራ አጋጣሚ ያገኜኋቸው ታላላቅ የኢትዮጵያ ሊቃናት እና ሊሂቃንንም በእጅጉ አመሰግናለሁኝ።
 
ለኢትዮጵያዊነቴ #ቴርሞ- ሜትር እንዳያስፈልገኝ አድርገው ከብክበው አንጸውኛል እና። ቾኩም ሰለዳውም ጥረቱ በዝልቅነት ተሳክቷል። ሰክኗልም። ተመስገን አማኑኤል አባቴ።
 
ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ መንፈስ ነው ብዬ የፃፍኩት በ2014 እኤአ ነበር። ከዛ በኋላ ነው በታሪክ ሙሁራን ሲገለጥ
ያዳመጥኩት። እኔ እራሴን እንደ ቤተ - ሙከራ ወስጄ በሠራሁት ናሙና ነበር ከሚስጢሩ ጋር የተገናኜሁት። 
 
ተጨማሪ ማንነቶችን ከውስጤ እንደዬዘመኑ ሊፈጠሩ ይችላሉ። የኮፐን ሃገንን ገድል ሳስብ የፆታ ማንነቴ፤ "የድምፃችን
ይሰማ" ንቅናቄ ይሁን የሬቻ ጭፍጨፋን በሚመለከት በትጋት ስሳተፍ ህብራዊነቴ፤ የአማራን ተጋድሎ ሳስተናግድ አማራነቴ፤
በቅድስ ተዋህዶ ፈተና ውስጥ እራሴን ሳገኜው ሃይማኖቴ ላይ ጎላ ብለው ሊወጡ ይችላሉ። ውህደታቸው እና ግባቸው ግን
ከምንጩ ይቀዳል። ምንጩ ዓራት ዓይናማ ነው ይህ ቀረህ የማይባል ሊሂቁ ኢትዮጵያዊነት።
 
ኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና ነው።
ኢትዮጵያዊነት ዩንቨርስቲ ገብተው ሊማሩት የሚገባ የዕውቀት ዘርፍ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ይሉኝታም ነው።
ኢትዮጵያዊነት የነፃነት #አብራክም መሐጸንም ነው።
ኢትዮጵያዊነት #አናባቢም፤ ተነባቢም ማንነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ሳይንስ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ህግ አክባሪነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ለእናት አገሩ ከየትኛውም ፍልስፍና ርዕዮት ዓለም በላይ ነው።
 
ኢትዮጵያዊነት ተፈሪ፤ ተከባሪ ማንነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ለሰብም ለተፈጥሮም ጥንቁቅ የሆነ ማንነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት አለኝ የሚለው የራሱ #መገለጫ ያለው ማንነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት የዊዝደም ማንነት ነው።
 
ኢትዮጵያዊነት ቅንጭብም፤ ጭልፍም ተደርጎ የሚደፈር ማንነት አይደለም። #ተፈሪ ነው።
ኢትዮጵያዊነት መኖርን ያሰለጠነበት የራሱ ድርጁ ኩነት ያለው #ክስተታዊ ማግኔት ነው።
ኢትዮጵያዊነት እራሱን የተዋሰ ማንነት አይደለም።
 
ኢትዮጵያዊነት ውስጥ #ብርኃን አለ።
ኢትዮጵያዊነት በልኩ ለልኩ የተፈጠረ ልከኛ ሰብዕዊ ማንነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት በፍትህ፤ በነፃነት፤ ምራቅ በዋጠ ሰብዕና የጨመተ ማንነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት የሚቀናበት፤ የሚያስቀናም ማንነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት መባረክም፤ መመመረቅም ነው።
 
ኢትዮጵያዊነት #አይዟችሁም ነው። ከፍ ሲልም #አጽናኝ።
ኢትዮጵያዊነት ጥሪኝ አለው። ይጠራል። ያባብላል፤ ያቆላምጣል፤ ይዳስሳል፤ ይዳብሳል፤ ያጽናናል።
ኢትዮጵያዊነት ጣዕሙ፤ ለዛው፤ ቃናው የውስጥ ፈውስነትን የሚለግስ ነው። ይህም ሲኖርበት ብቻ የሚገለጽ ጸጋ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ለዛው፤ ቃናው፤ ክህሎቱ በፈርኃ እግዚአብሄር ዶግማ እና ቀኖና መንበርነት የተፈጠረ ማንነት ነው።
የኢትዮጵያዊነት ንጥረ ነገር በግጥምጥሞሽ ሳይሆን በውህድ ጥልቃዊ መንፈስ የተፈጠረ ማንነት ነው።
 
#እርገት ይሁን።
 
ኢትዮጵያዊነት የአፍላ፤ የሳሙና አረፋ ወይንም የምራቅ የተኩረፍራፊ ግብታውያን የስሜት ክምችት የፈጠረው ሳይሆን፤ ምራቁን በዋጠ የሃሳብ ልዕልና እና ልቅና የተበጄ ማንነት ነው።
 
ኢትዮጵያዊነት ትናንትን ከዛሬ፤ ዛሬን ከነገ፤ ነገን ተነገ ወዲያ የሚያገናኝበት የራሱ ትውፊት ያለው የዳበረ ማንነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት እራሱን የሚገልጥበት፤ እራሱን የሚያብራራበት፤ እራሱን የሚተረጉምበት፤ እራሱን የሚያመሳጥርበት የተደራጄ
ፏፏቴያዊ የሃሳብ መቅኖ ያለው ማንነት ነው።
 
ኢትዮጵያዊነት በተገፋ ቁጥር ቀለም የሌለው ፔናነት መሆንን መጋፈጥ ይገባል። ለኢትዮጵያዊነት የበዛ አቅል፤ የበዛ አደብ፤
የሰከነ አዕምሮ እና የአፈጣጠርን ሂደት በጥሞና ማድመጥ ይጠይቃል።
 
ኢትዮጵያ በሌላ አቅሟ አስተምራ አብቅታ ተወቃሽ፤ ተጠቅጣቂ፤ ተገላይ የምትሆንበት ጉዳይ አይገባኝም። እንዲገባኝም አልፈቅድም።
የሚበጀው ወደ ውስጥ አይቶ እራስን መመርመር ነው። ኢትዮጵያ የአፍታ፤ #የለት ጉዳይ አይደለችም እና። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
02/10/026.
 
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ #በፊት ፈተናን #አሸንፎ የተፈጠረ ማንነት ነው።
See less

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።