ነገረ አርቲስት አንተነህ ትኽርቁ።

 #ዕንባ ሲሳነው። ዕንባ #በቃሽኝ ብሎ አፋጠጠኝ። ይገባዋልም።
#ስንት እኛወች አለን????

https://www.youtube.com/watch?v=L_8wH3-eBTU
«አርቲስቱ በወልቂጤ ከተማ በግፍ ተገደለ #rip #antenehe #ethiopiamovie #seyfufantahun»

• ድምጽ አልባወቹ የኢትዮጵያ እናቶች ያለ ሃይማኖት ልዩነት በወል ሱባኤ ቢገቡ። ፈጣሪን
ቢለምኑ።
• አላሃቸውን ቢማጸኑ የሚል ሃሳብ በትህትናና አቀርባላቸዋለሁኝ።

"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም
ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውልም።" ዛሬ ዕውን ሆኖ ያጋጠመኝ ክስተት ነው።

#ምዕራፍ ፳።

የዕንባ ጠብታ
የቁስለት ጠብታ
የምሬት ጠብታ
እኔን እያማታ
ዕንባው እና ማታ
ለመነ ምህረትን ሳያመነ ---- ታታ ---- ታታ።

#ዛሬ ልዩ ቀኔ ነው። ማስተዋልን ከተሰጠኝ በላይ እንዳስተውል የሆንኩበት ዕለት።

#ውስጤ ለውስጤ ጥያቄው እና መልሱ።

ዛሬ ቀጠሮ ነበረኝ - ከሰዓት። ግን ማስተዋልን የበለጠ እንዳስተውል የእዮር ስጦታን አገኜሁኝ። በዝምታ ለማሳለፍ ወስኜ ነበር። ፌስቡክም ላለመግባት። ብሎጌንም ላለመጎብኜት።

#ልለምናችሁ። እናንተም እሺ በሉኝ እባካችሁን? ግን ደህና አደራችሁን ማህበረ ቅንነት።

የጥዋት ጉዳዬን ከውኜ ዜና ፍለጋ ላይ እያለሁ ሌላ ገጠመኝን አስተናገድኩኝ። ማህበረ ቅንነት እኔን ጨምሮ ብዙ የተጎዱ ነፍሶች፤ የታመቀ ሃዘናቸውን ዋጥ አድርገው የያዙ በቤታችን ቤተኞች አሉ። ዕንባማ ወገኖቻችን ለካ አብረውን አሉ። ይገኛሉ። ስለሆነም በምንጽፈው፤ በምንሞግተው ሃሳብ ላይ ብርቱ #ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል። የጽናት የውሃ ልክ የሆኑ ቤተኞቻችን አሉ። በህመማቸው ላይ ሌላ መከራ አንጫንባቸው። አደራ።

ያው ፔጃችን ከፎቶ ላይ ኤክስ አይፈቀድም። ስድብም ፈጽሞ #የተከለከለ ነው። ለጥሞና ጊዜ ረጅም ስለምወስድ ያን ጊዜ ሊገጥም ይችላል። ከቤታችን ካለሁ ግን ካየሁ ዘለፋ ስንብት ነው። ብዙ ደክሜያለሁ ቤታችን በሞራልም፤ በሥርዓትም የተስተካከለ ቁመና እንዲኖረው ለማድረግ። ጨዋ፤ የጨመተ ተግባር ልፋቱ ካልቀአ። ዛሬ ያገኜሁት ልዩ ስጦታ ደግሞ ፔጃችን #የአጽናኝነት ሮል እንደ መደበኛ ተግባር ይኖረው ዘንድ ነው።

የቅኔው ልዑል ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን የወንድ ልጅ ዕንባ በውስጡ መታመቁን ተቀኝቶበታል።

"ወንድ ብቻውን ነው የሚያለቅሰው"

… መሽቶ የማታ ማታ ነው ሌት ነው የወንድ ልጅ እንባው
ብቻውን የሚፈትነው (እሳት ወይ አበባ ገጽ 102-3)

"……… ያኔ ነው ወንድ ዓይኑ የሚረጥብ
የብቻ እንባ ወዙ የሚነጥብ።
ብቻውን ነው ብቻውን ነው……
የእንባ ጨለማ ለብሶ ነው
ወንድ ልጅ ወዙ እሚነጥበው።"

ሁለቱም ገጠመኝ ተዋህደው ነው ዛሬ የገጠመኝ። የሚገርም ገጠመኝ። አርቲስቱ ከእንባ ጋር አድጎ እንባ ሲሆን፤ ሌላ በሃዘን የተጎዱም መከራቸውን ዕንባቸውን እያፈሰሱ ችለው አገሬ ኢትዮጵያ ይላሉ ………የጽናት የውሃ ልክ።

በዚህ የህማማት ዘመን ግን ተብዕት እንባቸውን እያነቡ ከዕንባ ጋር መኖርን እየተጋፈጡ እንዳሉ ተረዳሁ። ዛሬ የሰጠኝ ታላቅ ዕድል እና ተመክሯዊ ሁነት ከወትሮው የተለዬ ቅን፤ ግልጽ እና መምህር ነበር። "እግዚብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል ሰው ግን አያስተውለውም።" ይህን የህይወት ቃል በዕውን የተሰጠኝ ያህል ተሰማኝ። ቃሉን የማዘወትረው ቃልም ነው።

በክስተቱ ውስጥ ሆኜ ዕንባዬ አቅም አነሰው። አፋጠጠኝ። ይገባዋልም። ለምን? የሰርክ ሆነ። ሁሉ ቦታ ማን ይገኛል ቢባል #ዕንባ ነው። የሚሰማው፤ የሚታዬው ዕንባ። ዕንባ አያልቅም እላለሁኝ። ዛሬ ዛሬ ግን እያቃተው ይመስለኛል። መኖር እራሱ ዕንባ ሲሆን እሰቡት።

ዛሬ በገጠመኝ ሁነት ከቀጠሮ መቅረቴን ደውዬ ገልጬ፤ በጥሞና ላሳልፍ ፈለግሁኝ። ግን አገር ዓለም እንዴት እንዳደሩ ዜና ማድመጥ ፈለግሁኝ። ዕንባ ጋር ነው የቆየሁት። #የጠበቀኝም ዕንባ ነው።

#ጠይም ዕንባ።

ጠይም ከሚባል ሚዲያ፤ ጎራ ከሚባል ሚዲያ ተመሳሳይ ፎቶ ተለጥፏል። ጠይምን አስቀድሜ ሳዳምጥ ፈቃዴን ሳይጠይቅ ያው እንደ ልማዱ ፈሰሰ። አልቻልኩም። አቁሜ ጠበቅኩኝ።

አርቲስት መፍጠር #በሩ ተዘግቷል። ቀደምቶቹ ተኝተው ሲነሱ ሳይሆን በዛው ሲቀሩ አንጋፋው፤ የማይተካው #እነኩራን፤ ሆስፒታል መኪናቸውን ሾፍረው ሄደው ሬሳቸው ተጭኖ የሚመጣበት እንደ አርቲስት ማንዲጎ አፈወርቅ እና ሌሎችንም ዕንባ አሰንቀውናል።

ምኑ ማት ይሆን የወረደብን?
ምኑ እርግማን ይሆን የፈሰሰብን? ሃኪሞች እንደወጡ ይቀራሉ። በጎጃም በጎንደር የሆነው ይህ ነው። ወጣቶች አገር ሰላም ብለው የቻሉትን ያህል ሲተጉ በአጭር ገዳያቸው ሳይታወቅ ያልፋሉ ጎንደር ከተማን ማንሳት ይቻላል፤ በቅርቡ ደግሞ ጉራጌ ዞን ይህንን መሰል መራራ ነገር እየተደጋገመበት ነው። ምን #እርግማን ይሆን እየዘነበብን ያለው።

ስንት የገዳይ ቲም ይሆን ያለው????
ስንት እኛወችስ አለን?ይህን እየሰሙ ያሉ የኢትዮጵያ እናቶች ስለ ማህጸናቸው ሱባኤ ሊገቡ ይገባል። አምላካቸውን አላሃቸውን በቃ እንዲላቸው ሊጠይቁት ይገባል።

አርቲስት #አንተነህ ትኽርቁ እንዳለፈ ነው ሚዲያወቹ የሚገልጹት። አስተዳደጉ ካለ ወላጅ፤ ካለ እህት የህዝብ ልጅ ሆኖ ነው። ያን ግማድ አሸንፎ #ተዋናይ መሆኑ እራሱ የታምር ነው። ሃዘኑን ለመርሳት እስፖርት አጽናኙ ሆነ፤ እኔ መራራውን ሃዘን ለመርሳት ፌስቡክ መድህኔ እንደሆነው ሁሉ።

በመከራ ብቻውን ያደገ፤ በልፋት ዕጣ ነፍሱን ያደገ፤ ወላጆቹን በወል ያጣ፤ እህቶቹን ሁሉንም ያጣ ታታሪ፤ ትጉህ #ማተበኛ፤ ባለ #መስቀል ሞት አጥምዶ ይህን የመሰለ ሁለመናው የሚያጓጓ ልጅ ኢትዮጵያ አጣች። ኢትዮጵያ ታልቅስ ይህን የመሰለ ምንም የማይጎድለው ዕንቡጥ የጥበብ።

ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ለልጆቿ #እረኝነቱን መቼ እንደምትጀምር፤ እናትነቷን መቼ እንደምታስከብር ቅብዓዋን የሰጣት አማኑኤል አባቴ ይወቀው ይጠይቃትም። ስንት ሰማዕታት ልጆቿን በመገበር ላይ እንዳለች።

እንደ እራሴ ውስጥ ነው ያዬሁት ወጣቱን። እስከመቼ ለሚለው የራሄልን ዕንባ ያደመጠ አምላክ የኢትዮጵያ እናቶችን ዕንባ ያዳምጥ ዘንድ እለምነዋለሁኝ።

ሚዲያወች በሌለ፤ ባልተፈጠረ ሁነት ከዛም አለ እያሉ የሚሠሩት ዜና ነው የጠንቁ ገፋፊ። ቢሆን እንኳን እንዲህ ዝርግ የሆነ በሚዲያ ፖሊሲ መከተል አረመኔነት ነው። ሰው ለማትረፍ እንትጋ። የራስን የጋብቻ ዝምድና ሳይቀር ከአገር እያስወጡ፤ ባለቤት ለላቸው ወጣቶች መቃብር መፍጠር አያስፈልግም ነበር። ጥንቃቄ በብርቱ ያስፈልጋል። ሰው የጀንበር የእጅ ሥራ ውጤት አይደለም እና።

እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ አርቲስት አንተነህ #ጤናው የተሟላ አይደለም። ባላንሱን መጠበቅ አይችልም ነበር። ይህን የሰማችሁ፤ ያወቃችሁ አቅም ያላችሁ የአገሬ ልጆች ወደ ውጭ ወስዳችሁ ልትረዱት ይገባ ነበር። በዚህ ዙሪያ የሚተጋው ውጪ ሰንሰለት ዩቱብ ነው። እንደዚህ ዓይነት ገጠመኞችን ለመቅደም #ቀድሞ መገኜት ያስፈልግ ነበር። ምንም እንኳን ሁሉም ክስተት የፈጣሪ ፈቃድ ቢሆንም።

ወጣቱ አርቲስት #ከሳቅ ጋር ሳይገናኝ፤ ከመጽናናት ጋር #ሳይታረቅ ሁለመናው፤ ውስጡ ጥቁር እንደ ለበሰ መራራ ስንብት። #ኦ! ፈጣሪ ሆይ! መቼ ምህረት ለኢትዮጵያ ትውልድ ትልክ ይሆን???? ይህን ዘመን ከሞት ያመለጠ ሎጋ ዕድለኛ ነው።

ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።

ኢትዮጵያ ሆይ ጽናት መቀነቱን ይስጥሽ። አሜን።

ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
30/10/2026.

ኢትዮጵያ ሆይ! ጽናቱን ይስጥሽ። አሜን።
ይህን ማት የምትቋቋሚበት አቅም ፈጣሪ ይስጥሽ። አሜን።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።