«ሚስጢር የባቄላ ወፍጮ አይደለም።»
«ሚስጢር የባቄላ ወፍጮ አይደለም።» ራሺያ በእኩል ኢትዮኤርትራን #ከውስጥ ታቀርባለች። ሚስጢር ነው።
#ለፈላስፊት ኢትዮጵያ ለመሰጠቷ፤ ለብቃት ልዕልናዋ፤ ለልቀት ቅብዓዋ የመንፈስ ዘቢደሯ ነኝ።
"አቤቱ ልቤ አይታበይብኝ።" አሜን እላለሁኝ። እኔው።
(መዝሙር ምዕራፍ ፻፴ ቁጥር ፩)
• «ሩሲያ በኢትዮጵያ እና ኤርትራን መካከል 'ታማኝ' አደራዳሪ መሆን ትችላለች? ለምንስ
ማደራደር ፈለገች?»
#ምዕራፍ ፳።
ራሺያ ሊቃናቶቿ፤ መሪዋ፤ ህዝቡም ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ አገራት እና ህዝቦች ቀና ልቦና አላቸው። ከውስጣቸው እንደሚያቀርቡን አውቃለሁኝ። በስደትም የቤተሰብ ያህል ነው እኔን የሚገጥመኝ።
#ለምን?
"ሚስጢር የባቄላ ወፍጮ አይደለም።" ይላሉ ባለቅኔ ጎንደሮቹ። በኢትዮጵያም ይሁን በኤርትራ በኩል ለራሽያ ያለው የቅርበት ሁኔታ እንደ መሪወቹ ሊለያይ ይችላል። ራሺያወች ግን ለሁለቱም እኩል አክብሮት፤ እኩል ወዳጅነት አላቸው።
በኢትዮጵያ የብልጽግና ሹማምንቶች ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ የሚበልጡባቸው ሌሎች አገሮች እንደሚኖሩ አስባለሁኝ። ቅድሚያ የሚሰጣቸው፤ በአቀባበል ይሁን በትኩረት የበለጠ ክብር የሚሰጣቸው እንዳሉ ይሰማኛል።
በማንኛው የመንግሥት እርምጃወች ዘንድ ማን ይከፋል? ማን ደስ ይለዋል? ተብሎ እንደሚተመን ይገባኛል። ይህም ሆኖ የራሽያ ሊቃናት፤ የራሺያ መሪወች፤ ፕሬዚዳንት ፑቲን፤ ህዝቡ ሁሉም ለእኛ የውስጥ የሆነ ውስጥነት አላቸው። ለምን? #ሚስጢር ነው።
#ድርድር እና ስኬቱ በግምቱ - በስሱ።
ዜናው ለእኔ የምሥራች ነው። በአጀንዳ መያዙ። ዛሬ BBC ሙሁራን አነጋግሮ ዕይታውን ዘግቧል። እኔም ሙሉውን አያይዠዋለሁኝ። ለምሳሌ ለዩክሬን እና ለራሽያ ሰላም የቀድሞ የጀርመን ካንስለር ወ/ሮ አንጌላ ሜርክል (ዶር.) ሊያሳኩት ይችላሉ ብዬ አስባለሁኝ። ዓለም ዕድል ቀንቶት በቀጣዩ ተመድ ምርጫ ክብርቷ ቁልፋን ቦታ ቢያዙ የዓለማችን የፖለቲካ ባህሪ ተፈጥሯዊ መልኩን የማምጣት አቅም ሊኖረው ይችላል ብዬ በጽኑ አምናለሁኝ። መሪነት ስኬቱ ከቅብዓው ይፈልቃል እና።
የተከበሩ ክብርት አንጊላ ሜርክል ሥልጣን ላይ ቢሆኖ ኑሮ 90% የራሺያ እና የዩክሬን ጦርነት አይጀምርም ነበር። አሁንም መፍትሄው ያለው በዓለም ፖለቲካ ሥልጡን፤ እናታዊ፤ #ቅርባዊ፤ ሰዋዊ ርህርህርት፤ የፖለቲካ ክህሎት ባላቸው በወ/ሮ አንጌላ ሜርክል (ዶር) ድርድሩ በሳቸው መሪነት ቢጀመር ይሳካል ባይ ነኝ። ደረጃውን የጠበቀ ስለሆነ።
በኤርትራም በኩል ቅርብ ከሆነ አገርበራሺያ ጉዳዩ ቢያዝ የሚከፋቸው አይመስለኝም። አሁን ከሆነ የተመድ የሰላም አስጠባቂ ኃይል እንዲኖር ሁሉ እንደ ጠየቁ ሰምቻለሁኝ።
ኢትዮጵያን በገመቱት ልክ አቅመ ቢስ ሆና አልተገኜችም። በህወሃት የሚመራው ማዕከላዊ ዕዝም የጠበቁትን ዓይነት ስኬት በአጭር ጊዜ አላስገኜላቸውም። ዘመኑን ማስተዋል ይገባል። ለየትኛውም እርምጃ ዘመንን ማድመጥ ይገባል። ዘመንን ስል የዘመኑን የፖለቲካ ባህሬ እና የኃይል አሰላለፍ ማለቴ ነው። የአትኩሮት ምጣኔም።
እንዲያውም ሁለቱም ዕድለኞች ናቸው። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ማለቴ ነው። በዚህ ውጥንቅጥ ወቅት "ላገናኛችሁ" የሚል ኃያል አገር መገኜቱ የዘመን ስጦታ ነው - ለእኔ። ባይገፋት ወይንም ዕድሉን ባይደፋት ይበጃል።
ይህን ሂደት #ግብፆች የሚፈልጉት አይመስለኝም። እንዲያው ሁለቱ ይሁንታ ሰጥተው ቢጀመር ንግግሩ፤ ኤርትራውያን አፍርሰው እንዲለዩ የተለጠጠ የቅድመ ሁኔታ ሊያማክሩ ይችላሉ የግብጽ ሊቃናት ለኤርትራ። ንግግሩ #ጠፍር ክርር እንዲል የግብጽ ሊቃናት ልያደርጉ ይችላሉ ብዬ አስባለሁኝ። የግብጽ የፖለቲካ ሊቃናት ለኢትዮጵያ የእንቅፋት አምራች ካንፓኒ ናቸው።
ይህን ሃሳብ ይዘን ወደ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ስንሄድ ራሺያ ትክክለኛው ምርጫ ነው ብዬ አምናለሁኝ። ይሁንታ በሁለቱ ወገን ከተገኜ ለንግግሩ መቀራረብ ይሁን ለቀጣዩ ለድርድሩ ሂደት ስኬት የራሺያ ሊቃናት ሊያሳኩት ይችላሉ ብዬ አስባለሁኝ።
ተመስገን ነው አሁን ከሆነ የኢትዮጵያ የባህር በር እና የወደብ አስፈላጊነት ጉዳይ ግሎባል #ዕውቅና አግኝቷል። በፊት ጊዜ ያሳስር የነበረ ዕውነት ዛሬ የንግግር መግቢያ ሆኗል። ሁሉም ይናገረዋል። ደጋፊውም ተቃዋሚውም።
ለዓለም የደህንነት ዋስትና የቀይ ባህር ተዋሳኝ ይሁኑ ቅርበት ያላቸው አገራት አክሰሱ ቢኖራቸው የተሻለ አቅም መፍጠር የሚቻል ይመስለኛል። ለቀንዱ አገራት፤ ለመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካም ይሁን ለአህጉራችን አፍሪካም፤ በተጨማሪም ለግሎባሉ ፖለቲካም ጠቃሚ ይመስለኛል የኢትዮጵያ #ቤተኝነት። የኢትዮጵያ ስፕሪት ረቂቅ ነው፤ መድህንም።
#አሰብ እና እኛ።
አሰብ የወሎ ክፍለ አገር ነው የነበረው በእኔ ዕድሜ። ኤርትራም የኢትዮጵያ ነው የነበረችው በእኔ ዕድሜ። ለኤርትራ ሊቃናት አያያዝ ልዩ ነበር። በኢትዮጵያ ፖለቲካ የኤርትራ ሊቃናት #VIP ነበሩ ማለት ይቻላል። አራጊ ፈጣሪ እነሱው ነበሩ።
አሁን አገር ሲሆኑ የሚፈልጉት የበላይነት ልክ ከኢትዮጵያ ጋር በነበሩበት ደረጃ የመሪነት #ሮል ይኑረን ይመስለኛል። ሚዲያወቻቸው ፕሮ ኤርትራውያን ኢትዮጵውያን ሳይቀሩ የበታችነት ይናፍቃቸዋል። ዝቅታን ያልማሉ።
ሁሎችም አጀንዳቸው ቀን ከሌት ኢትዮጵያ ናት። እኔ አጀንዳዬን ኤርትራን አድርጌ አላውቅም። ከልጅነት ጀምሮ ፖለቲካውን አውቀዋለሁኝ። ግን አገር መሆን እስከፈለጉ ድረስ ፖለቲካቸው ላይ መተራመስ አልሻም። የማልሸሽገው ግን የምር ከውስጤ በነበሩት ልክ ግን አሉ። አሳድገውኛል። ቀኜ ናቸው ለቤተሰቦቼም። ጥሩ ጊዜም አሳልፈናል።
ሁለቱንም አሰብን ይሁን ምጽዋን የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካል የሰማይ ስጦታን በህውሃት አማካኝነት ጠቅልላ እንድትወስድ የተደረገችው ኤርትራ ምን አተረፈችበት? ይህ ጉልላታዊ ጥያቄ ነው። ዓለም እራሱ ኤርትራን ከኢትዮጵያ በመነጠሉ ከሰረ? ወይንስ አተረፈ? የዓለም ፖለቲካ ዕውነቱን ቁጭ አድርጎ ሊገመግመው ይገባል።
ውዶቼ ----- #ምን ሆነ መሰላችሁ?
ህገ መንግሥት ተሻሽሎ ወደ ፌድራሊዝም የደርግ ሥርዓት ሲሸጋገር፤ ክፍለ አገራት ከሁለት ከሦስት ተሸነሸኑ፤ #ራስ ገዝ የሚባል ነገርም መጣ። አሰብ፤ ትግራይ፤ ኤርትራ፤ ራስ ገዝ ሆኑ። ይህ ማመቻቸት ለህወሃት እና ለሻብያ አቀባበል የኢሠፓ ፖሊት ቢሮ የሰራው የተሠወረ #ገመና ይመስለኛል። ኢትዮጵያን በጀርባ የማሳረጃ ስሉ ማጭድ ነበር። ይህ ሁሉ እልቂት ስክሪፕቱ ከዛ ጋር የተያያዘ ነው።
#ቢስማሙ ግን ………
1) ይዘልቃል ወይ? ሌላ ፈታኝ ጉዳይ ነው። በድፍረት በእርግጠኝነት መልስ የማይገኝለት።
2) እንዲያው ቸር እናስብ እና በየትኛውም ዘመን ቢስማሙ፤ የኤርትራ ኢትዮጵያን በበላይነት የመምራት ናፍቆት ካልተሳካ የፈለገው የስምምነት ዓይነት ይቀጥላል ወይ? ----- ይህም ውሃ ያዘለ ተራራ ነው። የታመቀ ፍላጎት ስላለ።
3) የኤርትራ የፖለቲካ ሊቃናት ከኢትዮጵያ ራስ የመውረድ ቁርጠኛ ውሳኔ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ ወይ? ለኤርትራ የፖለቲካ ሊቃውንታት አጀንዳቸው እኮ ኢትዮጵያ ብቻ ናት። የራሳቸው ጉዳይ ስንት የቤት ሥራ እያለባቸው።
4) ኤርትራውያን በየትኛውም የንግግር ማዕቀፍ #አውጥተው መናገር የማይፈቅዱት #የተሠወረ መሻት አለ። ታዛዥ የኢትዮጵያ መሪ ይሻሉ። ከኤርትራውያን ዝቅ ብሎ መኖር የሚችል በባዕቱ ኢትዮጵያዊ ይመኛሉ። ይህን ስውር ፍላጎት ማስታረቅ ይቻላል ወይ?
ሌላው የሚገርመኝ ነገር የኤርትራ መንግሥት፤ የግብጽ መንግሥት ከጎረቤት አገራት የባህር በር፤ የወደብ አክሰስ ኢትዮጵያ እንዲኖራት በፍጹም አይፈልጉም፤ ያሰናክሉታልም። ኢትዮጵያ ሰላም ማጣቷ ዋነኛ የመንግሥታቱ ፕሮጀክት ነው። ለምን? #ስለሚቀኑባት ነው።
የኢትዮጵያ መሪወቿ ባያከብሩትም፤ ኢትዮጵያ ያላት ስበት #ማግኔታዊ ነው። #ተሰጥቷታልም። መከበርንም ተሸልማለች። ግርማዋ የተደላደለ እና አስፈሪም ነው። "ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም። "ይላሉ ጎንደሬወች።
መቸውንም ቢሆን ኢትዮጵያ #ተሸናፊ አትሆንም። እኔ ሥርጉተ©ሥላሴ በምንም ሁኔታ፤ በየትኛውም ጊዜ የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ አገራት የሚያዘጋጁት #ታዛዥ አደግዳጊ መሪ ፈላስፋዋ እናቴ እንዲኖራት አልሻም።
በፍፁም ኢትዮጵያ በኤርትራ ሥር፤ በፍፁም ኢትዮጵያ በግብጽ ሥር #በሞግዚት አስተዳደር ሥር እንድትሆን አልሻም። ለአገሬ ኢትዮጵያ ለተሰጣት ብቃት፤ ለአገሬ የመሰጠት ልዩ ጸጋ፤ ለመክሊቷ፤ ለቅብዓዋ፤ ለልቅና እና ልዕልናዋ የመንፈስ #ዘብይደሯ ነኝ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን። ክብረቶቼ ሆይ! ዛሬ ሙሉ ቀን አብረን አረፈድን፤ ዋልን፤ አመሸን። ቀሪው አዳር ነው። ሌሊቱ ብሩክ፤ ቅዱስ ይሁንላችሁ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
29/10/2026.
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት፤ #ፈተናን #አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
#የBBC ዘገባ።
"የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ሞስኮ የሚገኙት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች "ፍላጎት ካሳዩ" ለማደራደር ዝግጁ መሆኗን ሩሲያ አስታውቃለች።
ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ በሚካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባዔ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች በመስከረም ወር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ሙሉ በሙሉ ካቋረጡ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ መድረክ የሚታደሙበት ነው።
ከጉባዔው አስቀድሞ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ ያደረጉት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌ ላቭሮቭ፤ ሁለቱን አገራት የማደራደር ሚናን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሩሲያ ኢትዮጵያን እና ኤርትራን በማሸማገል ሚናዋ ምን ሊሆን ይችላል? የትኞቹ የድርድር ነጥቦች ሊነሱ ይችላሉ? ውጤታማስ ሊሆን ይችላል? በሚሉት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የፖለቲካ እና ደኅንነት ተንታኞችን ምልከታቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የሚኖር ድርድር ውስጥ ቁልፍ ከሚሆኑ ነጥቦች መካከል የባሕር በር ጉዳይ በዋናነት ይነሳል።
ሴርጌ ላቭሮቭ ከጋዜጠኞች ከቀረበላቸው ጥያቄ መካከል ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ለምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ሩሲያ ምን ዓይነት ምላሽ ትሰጣለች? የሚለው ይገኝበታል።
እሳቸውም የሁለቱን አገራት ጉዳይ በተመለከተ "እንደተረዳሁት እየተነጋገርን ያለነው ባሕር በር ስለማግኘት ነው። ሁለቱ አገራት በአሁኑ ወቅት የተቋረጠውን ግንኙነታቸውን እንዲያድሱ ፍላጎት አለን" ሲሉ መልሰዋል።
የቀይ ባሕር ጥያቄ
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንዲሁም ተመራማሪ ዶ/ር ሙከረም ሚፍታህ፤ በሩሲያ በኩል የባሕር በር ጥያቄ በኩል ያላት አቋም "ያለ ምንም ጥርጥር የሁሉቱን አገሮች ጥቅም ወይም ጥያቄ ችግር ውስጥ በሚከት መንገድ ምላሽ የሚሰጥ እንደማይሆን" ይናገራሉ።
ሁለቱንም "የሚያስከፋ" በሆነ መንገድ ለባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንደማትሰጥም ይገልጻሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኝ እንደሚሉት፤ ሩሲያ ሁለቱን አገራት ለማስታረቅ የፈለገችበት ዋና ምክንያት "በቀይ ባሕር ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ስለፈለገች" ነው።
የሩሲያ የቀይ ባሕር ድርሻ ከሌሎች የምዕራብ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ሩሲያ "አስታራቂ" መሆን እንደማትችልም ባለሙያው ያስረዳሉ።
ለዚህም ምክንያት ያሉት ሩሲያ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኤርትራ የበለጠ ወዳጅ መሆኗን ነው። ኢትዮጵያም ከሩሲያ ይልቅ ምዕራባውያን እንዲያስታርቋት እንደምትፈልግ ያምናሉ።
የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ዲፕሎማት እና ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያ አቶ ባይሳ ዋቅወያ በበኩላቸው ሩሲያ ሁለቱ አገራት "ችግር ውስጥ እንዳይገቡ በማደራደር ትክክለኛዋ አካል ነች" ይላሉ።
"ከሩሲያ መንግሥት ይልቅ ከኤርትራ ሕዝብ እና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንዲሁም ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከኤርትራ መንግሥት ጋር የሚቀራረብ የለም" ይላሉ።
ሩሲያ ለምን ማደራደር ፈለገች?
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ፤ አሁን ላይ በሁለቱ አገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አለመኖሩን ጠቅሰው "ይህ ሁኔታ ከዚህ ቀደም አንድ አገር እንደነበሩ ሁሉ፣ ለረዥም ጊዜ በጎረቤትነት አብረው ለኖሩ ሁለት አገራት መልካም አይደለም" ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አገራቸው "ከረዥም ዓመታት በፊትም" የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሻሻል ጥረት ማድረጓን አስታውሰዋል።
ዶ/ር ሙከረም እንደሚሉት፤ ሩሲያ በሁለቱም አገሮች ዘንድ "አንጻራዊ የሆነ ጠንካራ ቅቡልንት እንዳላት" ታስባለች።
ላቭሮቭ ያንን መሠረት አድርገው፤ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት እንዳይሻክር ወይም "ወደ ግጭት እንዳይሄድ" ማድረግ ይሻሉ።
በተለይም የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛቶች መግባታቸውን ተከትሎ ሁለቱ አገራት ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
ኢትዮጵያ ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ወታደሮቹ ከግዛቷ እንዲወጡ ጠይቃለች።
ኤርትራት በምላሹ ለምክር ቤቱ በጻፈችው ደብዳቤ ኢትዮጵያ ወረራ ለመፈጸም ሽፋን እንደፈለገች ከስሳለች።
ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ያቋረጠችው ከኤርትራ ጋር ብቻ አይደለም። በኢትዮጵያ ታጣቂዎችን በመደገፍ ከከሰሰቻት ግብፅ ጋርም ዲፕሎማሲያዊ ቁርሾ ውስጥ ገብታለች። ኤርትራ እና ግብፅ ክሶቹን አስተባብለዋል።
አሁን ላይ የህወሓት ኃይሎች ከፌደራል መንግሥቱ እና አጋሮቹ (የትግራይ የሰላም ኃይሎች) ጋር ግጭት ውስጥ ቢገቡም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ይፋዊ ውጊያ አለመኖሩን ዶ/ር ሙከረም ይጠቅሳሉ።
ላቭሮቭ ያቀረቡት ሐሳብ "ልዩነቶቻቸውን መፍታት ባይችሉም፣ ይሄ ልዩነት አገርሽቶ፣ ሁለቱ አገራት ግልጽ ጦርነት ውስጥ እንዳይገቡ በማገድ ሚና እንደሚኖረው" ያስረዳሉ።
ሩሲያ በድርድር ስኬታማ ልትሆን ትችላለች?
ላቭሮቭ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የሚነሳ "ማንኛውም ችግር መልካም ፈቃድ ላይ ተመሥርቶ" በሚደረስ እና "ፍላጎቶችን በሚያማክል ስምምነት መሠረት ይፈታል" ሲሉ ተደምጠዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የደኅንነት ተንታኝ፤ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረገድ፣ ምዕራባውያን አገራት ከኤርትራ ይልቅ ከኢትዮጵያ ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዳላቸው እና ኤርትራ ከምዕራቡ ዓለም ይልቅ ከሩሲያ ጋር ቅርብ እንደሆነች ያምናሉ።
"ኤርትራ ብቻ ሳትሆን የኤርትራ አጋር ግብፅም ሩሲያ የእርቅ ሽማግሌ እንድትሆን እንደምትፈልግ" ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ ግን ወደ ምዕራባውያን አገራት አሸማጋይነት ልታጋድል እንደምትችልም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጦር ጄቶችን ከሩሲያ ሲረከቡ ባደረጉት ንግግር፤ መሣሪያዎቹን ለመረከብ ተይዞ ከነበረው አንድ ዓመት ቀድመው እንዲያኙ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማዘዛቸውን ጠቅሰዋል።
"ፑቲን ኢትዮጵያን ይወዳሉ፣ ኢትዮጵያን ማገዝ ይፈልጋሉ" ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ ባይሳ ሩሲያ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ "በጣም ከፍተኛ ፍላጎት" እንዳላት ይገልጻሉ።
"እንደ ሩሲያ ኤርትራን እና ኢትዮጵያን ለማስታረቅ የሚችል ኃይል የለም" ይላሉ።
የሩሲያ መንግሥት "በሁለቱም ላይ ሥልጣን አለው" በማለትም "በእነሱ ላይ ጫና ሊፈጥርባቸው ይችላል" ሲሉ የማደራደር ሚናው ጠንካራ እንደሚሆን ያስረዳሉ።
ሩሲያ ከሁለቱ አገራት ለማን ትቀርባለች?
ዶ/ር ሙከረም የሩሲያ መንግሥት ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጋር በወታደራዊ እና ዲፕሎማሲ ዘርፍ ያለውን ግንኙነት ያነሳሉ።
ሩሲያ በንግድ ከሁለቱ አገራት ጋር እምብዛም ትስስር ባይኖራትም፤ በድሮን ቴክኖሎጂ፣ በወታደራዊ የደኅንነት መረጃ ልውውጥ ዘርፎች ግንኙነታቸው ጠንካራ ነው።
የግብርናውን ዘርፍ ስንመለከትም ሁለቱም አገራት ወደ ሩሲያ ምርቶች ይልካሉ።
ኤርትራ በሰብአዊ መብት ጥሰት እና በዴሞክራሲ ማጣት በምዕራባውያን የተጣለባትን ማዕቀብ ለመቋቋም ወደ ሩሲያ ትቀርባለች።
ኤርትራ በተባበሩት መንግሥታት የሩሲያን መንግሥት አቋም በመደገፍም ትታወቃለች።
እነዚህን እውነታዎች የሚጠቅሱት ባለሙያው፤ ሩሲያ "ግልጽ ጦርነት እንዳይነሳ ለማድረግ" አቅሙ እንዳላት ያስረዳሉ።
"ነገር ግን ቁርሾዎችን በመፍታት ወደ ሰላማዊ ግንኙነት ለማምጣት አቅም አላቸው አልልም" ይላሉ።
እንደ ሩሲያ ጠንካራ ጫና የማሳደር አቅም ያላት በሁለቱም አገራት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ባለቤት የሆነችው ቻይና ነች ይላሉ።
"ቻይና እና ሩሲያ አንድ ላይ ቢመጡ የሁለቱን አጋራት ቁርሾ የማጥፋት አቅም አላቸው። እርስ በርስ ከመጠፋፋት እርምጃቸውን እንዲያቅሙ የማድረግ አቅም አላቸው" ሲሉም ያስረዳሉ።
የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ አብዱራህማን ሰይድ፤ ሩሲያ ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ጋር ጥሩ ግንኙነት ካላቸው ጥቂት አገሮች አንዷ ናት ይላሉ።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሩሲያን እንደ "የረዥም ጊዜ ቁልፍ አጋር" አድርገው ይመለከቱታል።
ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር በብሪክስ ውስጥ ትገኛለች። በሰላማዊ የኒውክሌር ጉዳዮች እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይም አብረው ይሠራሉ።
ሩሲያ በዓለም ላይ ካሉት አምስት ድምጽን በድምጽ የመሻድ ኃይል ካላቸው አገሮች አንዷ መሆኗ "ሁለቱም አገሮች [ሽምግልናውን] ትኩረት እንዲሰጡ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ተናግረዋል።
ሩሲያ በቀይ ባሕር ጉዳይ መሳተፏ ሁለቱም አገራት "ትኩረት እንዲሰጧት" ሊያደርግ እንደሚችልም ይገልጻሉ።
ሩሲያ ለማደራደር ጥያቄ ባቀረበችበት መድረክ ላይ ኢትዮጵያ ከሞስኮ መሣሪያ መረከቧ ሌላው ነጥብ ነው።
አቶ ባይሳ ይህ "ከኢኮኖሚያዊ ዕይታ አንጻር" መታየት እንዳለበት ይናገራሉ።
ኤርትራ በሩሲያ ላይ ያላትን እምነት እንደማያዳክም የሚያምኑት ባለሙያው "ሩሲያ በታሪክ ኤርትራን ፈጽሞ አልጎዳችም" ይላሉ።
See less
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ