የዘመናት ትግል፤ የወጣትነት ህልም በስደት ለስደት #መነነ።

 

የዘመናት ትግል፤ የወጣትነት ህልም በስደት ለስደት #መነነ።
ክቡር ዶር ነገዴ ጎበዜ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ብራንድ ናቸው።
ኢትዮጵያ ሆይ! እግዚአብሄር ያጽናሽ። አሜን።
 
"መሬት ነህና እና ወደ መሬት ትመለሳለህ።"
 
 
 
ዛሬ ዕቅዴ ካቴና ላይ የሚገኙ ወገኖቼን እንዴት ሰነበታችሁልኝ ልል ነበር አገባቤ። በሌላ በኩል ነገ ፆመ ጽጌ መፍቻ ቀን ስለሆነም እንኳን አደረሰንን ላክልም ፈቃዴ ነበር። ግን ቀኑ ይዞ የጠበቀኝ #መርዶ ነው። 
 
ስለሆነም ዛሬም እንደ ትናንቱ አንጋፋ የስፖርት ሐዋርያ መራራ ስንብት፤ ዛሬም የአገር ዋርካ ፖለቲከኛ የሆኑ ወገኖቼን ስንብት በአካል ተገኝቼ አፈር ባላለብስም፤ ፔጄ ግን ይህን ተግባር ይፈጽም ዘንድ ፈቀድኩኝ።
 
የተከበሩ ዶር. ነገደ ጎበዜ በሥጋ መለየታቸውን ከአቶ እያሱ እያሱ ከሚል ፔጅ አገኜሁት። አዘንኩኝ። ዕውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ጉግል ጋር ተነጋገርኩ። የምር ዕውነት ነው። የተከበሩ ዶር ነገደ ጎበዜን #በአካልም አውቃቸዋለሁኝ። 
 
በአገረ ኢትዮጵያ ጉዳይ ሲባትሉ ዘገባ ልሰራ ሄጄ አግኝቻቸው ነበር። በተደጋጋሚ ለቀደምት ፖለቲከኞች የማቀርበው ጥያቄ የሴቶች እና የወጣቶች ተሳትፎ ላይም ሃሳባቸውን ቀረብ ብዬ ጠይቄያቸዋለሁኝ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ የከረባት እና የገበርዲን ብቻ መሆኑ ከሚያሳስቡኝ ጉዳዮች አንዱ ነው፤ በሌላ በኩል ተተኪ የወጣት ፖለቲከኞች መራቅም ያሳስበኛል። 
 
የተከበሩ ዶር ነገደ ጎበዜ በጸረ - ህውሃት ትግል ጠንከር ያለ ተሳትፎ ካደረጉት አንጋፋ ፖለቲከኞች ውስጥ አንዱ ናቸው። ህወሃትን በፋክት፤ በአመክንዮም ታግለውታል። ከኢተፖድህ መሥራቾችም ቁንጮው ክቡርነታቸው ነበሩ። አቶ እያሱ ከፃፋት በተጨማሪ ማለቴ ነው። በደርግ ጊዜም ታጋይ የነበሩ ይመስለኛል። እኔ ያገኜኋቸው ግን ህውሃትን ሲታገሉ ነበር።
 
የህግ ሰብዕና ያለው ወገን የተለዬ #ጸጋም አለው ብዬ አምናለሁኝ። በአኗኗሩም ሆነ በአካሄዱም። ዶር ነገደ ጎበዜ የበሰለ እና የሰከነ የፖለቲካ አቅም ነበራቸው። ስብሰባ ሲመሩም፤ ማብራሪያ ሲሰጡ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዥንጉርጉር ስለሆነ ያን ለአንድ ተልዕኮ በሚያስማማ አመክንዮ ለመምራት የገዘፈ ቻሌንጅ ይገጥማል። 
 
ይህን በትዕግስት አቻችለው፤ ቁጣም፤ ብስጭትም፤ ማፈንገጥም፤ ስብሰባ ረግጠው የሚወጡ ፖለቲከኞችን አስታግሰው፤ ከሥርዓት ውጪ ውክልና ያላቸውንም አስማምተው እንደ አንድ ብልህ ቸር ፐርሰን የመምራት፤ ኮኦርድኔት የማድረግ፤ አቅጣጫ የማስያዝ ልዩ አቅም አይቼም ነበር። ከሁሉም #የማድመጥ አቅማቸው አንቱ ነው። ኦዲዬንስንም - ያከብራሉ - ትንሽ ይሁን ትልቁን አቅለው አያዩም።
 
ሲበሳጩም ገጥሞኝ አያውቅም። ለጥያቄ እንኳን የሚበሳጩ ፖለቲከኞች ገጥመውኛል እና። የሆነ ሆኖ አገራችን ኢትዮጵያ በእጅጉ #ከምትናፍቃቸው የአመክንዮ ፖለቲከኞች አንዱም ነበሩ። እኔ በየትም ቦታ ስገኝ፤ ዝቅ ባለውም ይሁን ከፍ ባለው ብሄራዊ ጉዳይ ይሁን ዓለም ዓቀፍ ጉዳይ ውስጥን ለማየት የመፈለግ ዝንባሌ አለኝ። በማህበራዊ ህይወቴም እንዲሁ ነው።
 
 ፎቶንም የሰብም ሳይ ይሁን የምወደውን የጉም ፔንቲንግ ስመለከት፤ ከውስጡ በአትኩሮት የመመልከት መሻት አለኝ። የኢትዮጵያ አንጋፋ ፖለቲከኞችን ሳገኝም ሰፊው ጊዜዬ ውስጣቸውን ፍለጋ ማሰስን እመርጣለሁኝ። በዚህ ሂደት ዶር ነገደ ጎበዜ ለኢትዮጵያ ያላቸው ናፍቆት በአክብሮት እንደ ነበር አስተውያለሁኝ።
 
ውስጥን ፍለጋ ጊዜ የማጠፋውም ውጪው የውስጥ አቅምን፤ የውስጥ ክህሎትን፤ የውስጥ አወንታዊ ስፕሪትን የመግለጽ አቅሙ እንብዛም በመሆኑ። ከእኛ የቀደሙት በኢትዮጵያ እናትነት በማይደራደሩት ፖለቲከኞች፤ የኢትዮጵያ ቀደምት ፖለቲከኞች #የአመክንዮ ችግር አልነበራቸውም። ብቁ ርትዑ አንደበትም አላቸው። የመናገር አቅም አልቦሽ መሪነትን ማሰብ ስለማይቻል። ንግግር የማይችሉ የፖለቲካ መሪወች ለምኞታቸው ዳገት ስለሚጠብቃቸው። 
 
የሆነ ሆን ፍልስፍናው ርዕዮቱ በዘመኑ የፖለቲካ ባህሬ በሶሻሊዝም ኮሚኒዝም ቀደምቶች ቢማረኩም ፍልስፍናው፤ ሳይንሱ፤ ምርምሩ፤ ዕውቀት ፍለጋቸው አንቱ ነው። የወጣላቸው #አንባቢም ናቸው። ስልቹም ወረተኛም አልነበሩም - የጸኑ ናቸው። እራሳቸውን፤ ወጣትነታቸውን፤ የቤተሰብ ይሁን የአገር ናፍቆታቸውን ላመኑበት ዓላማ የመገበር ወይንም ኢንበስት ለማድረግም ልግስና አስተውልባቸዋለሁኝ።
 
ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ አሊ ወደ ስልጣን ሲመጡም ሳይዘገዩ #በፍጥነት #አወንታዊ አቀባበል ካደረጉላቸው ታላላቅ ፖለቲከኞች አንዱ ነበሩ። ልክ እንደ ተከበሩ ልዑል አስፋወሰን አስራተ ካሳ፤ የተከበረው አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ አንድ ሌላም የመኢሶን ከፍተኛ አመራር፤ በተጨማሪም ብዕረኛው "የብዕር አንጋቹ የእሱ አገላለጽ ነው።" አይበገሬው ጋሼ የሱፍ ያሲንም ነበሩበት። 
 
በወቅቱ ጽፌበት ነበር። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን የልብ ቁልፍ ያገኜ ዘመን ነው ብዬም አስብ ነበር። ግን ተስፋ በተስፋነቱ በአንድም በሌላም ሊቀጥል አለመቻሉ #የርግማን ይመስለኛል። በሰላም የተገኜ ሽግግር ጦርነት ናፈቀው።
 
የሚናፍቀው ሁልጊዜ #ያላባራ የሰው ማገዶነት መሆኑ ከውስጤ ያሳዝነኛል። በሰላም የተገኜ የእርቅ፤ የስምምነት የአብዛህኛው ይሁንታ ዕድል፤ የሰማይ #ታምር ነበር ለእኔ የህወሃት ፈቅዶ እራሱ ተሳትፎ መንበረ ሥልጣኑን በሰላም ማስከበር እግዚአብሄር የሰራው #ገድል ነበር። የተገኜበት መንገድ ዕድሉም ለእኔ እዮር ሠራሽም ነበር።
 
ባለመታደል ተለያይታችሁ ተለያዩ ተብለን ተረግመን እንዲህ ጠንዝሎ ያ ሁሉ የተደከመበት ተስፋ በስደት - ለስደት ተገብሮ፤ ወጣትነት ባክኖ፤ ሳቅ #በሳግ ተለውጦ የናፍቆት ራህብ አገላብጦ እንደ ቀቀለ መጠናቀቅ።
 
ለአገር አፈር ሳይበቁ የስደት ምናኔ ጋር መራራ ስንብት። የሚገርመው እና የሚደንቀው ኢትዮጵያን አቅለው፤ ክብሯን ልዕልናዋን #ጋግጠው፤ የሚፋለሟት እንደ አቶ ቀጀላ መገርሳ ይሁን ለአህጉር ኃላፊነት የበቁት እነ አቶ እንቶኔ ኢትዮጵያዊነትን #እየተጠየፋ፤ የፓርላማም የካቢኔም አባልነት የሚፏልሉት ሳስብ አዝናለሁኝ። እኩልነት፤ የአገር ልጅነት ከቶ ለመቼ ተቀጠረ ይሆን በኢትዮጵያ ፖለቲካ?
 
ከእኛ የቀደመው ትውልድ እያዬን ነው። መኖር እና መራራ ስንብቱ ለሁላችንም አይቀርም። አገር እንደራበው ተስፈኛው፤ ያ የኢትዮጵያ ገጠር ገበሬ ለዛ እና ወግ እንደተጓጓለት መራራ ስንብት። እንደ ወጡ መቅረት። 
 
እኛም መከተላችን አስበን ቢያንስ ጊዜያችን በክፋ ሃሳብ ቤተኝነት እንዳይበላ ልንጠነቀቅለት ይገባ ይመስለኛል። #ጸጸቱ ተሰደንም #መለያዬታችን ነው። ተሰደን እንኳን አንቺ ትብስ፤ አንተ ትብስ ለመባባል ፊት እንደ ተነሳሳን፤ አንዱ ሌላውን ባን እንደ አደረገ፤ ከይቅር መባባል ርቀን፤ ፍቅርን፤ ተፈጥሯዊ ጸጋችን አርቀን ወርርረን ግን መሬት ቻይ ናት እና ሁላችን እኛ በማንፈቅደው #የአንድነት ሳጥን ትረከበናለች። አሻም ማለት አንችልምና።
 
ታላላቆቹ፤ ሁሉ ያላቸው፤ ዕውቀቱም ተመክሮም የሰጣቸው ግን በስደት የሚኖሩት እራሳቸው ስብሰባ ጠርተው ሲተናኮሏቸው፤ ሲያሳድዷቸው፤ ሲያሳድዟቸው የነበሩትን ሁሉ ትንሽ ትልቅ ሳይሉ ይቅርታ ጠይቀው ባአንድ ማዕድ #ባርኮትን ቢፈጽሙ ይቅር ቢባባሉ፤ ዛሬም፤ ነገም ይስቃሉ። ዛሬም ነገም ይከብራሉ ዕለታቱ ይሁን ዘመናቱ። 
 
ስለሆነም ተተኪው ትውልድ እኛ ባለፍንበት #ፍትልትል ጎዳና መኖሩ፤ ዘመኑ፤ ተስፋው እና ራዕዩ #ቅርጥም ብሎ እንዳይበላ ልንጠነቀቅ ይገባል።
 
ብስጭቱን - ተግ አድርገን፤ መዘላለፋን - አስታግሰን፤ ቂም እና ቁርሾ ሃራም ብለን፤ ህግ መተላለፋን አቁመን እላፊያዊ ፋስ አይሎ ስለማይም፤ ታግሶ - ማለፍን፤ ችሎ - #ማስቻልን በታረመ አንደበት እና በሰከነ ሰብዕና በፈርኃ እግዚአብሄር እና በፈርሃ አላህ እራሳችን ገርተን ሲሆን ሲሆን መስዋዕትነት ባይኖር፤ በስተቀር መስዋዕትነት የቀነሰ አማራጮችን ማየት የሚገባ ይመስለኛል። 
 
የኢትዮጵያ እናቶች የልጆቻቸው ዓይን እንደ ናፈቃቸው ያልፋሉ። ያ የኢትዮጵያ እናቶች መሃጸን ቄራነት ግን ዛሬም በገፍ #ለእርድ እየቀረበ ነው። ለሞት የሰው ልጅ እንደ #በረከት የሚሰጥበት ዘመን ላይ ነን። 
 
መታበዩ፤ መስቃውማ፤ መዘላለፋ፤ አንዱ አንዱን ማቃለሉን ሁሉ ገምግመን ከእኛ የተሻለ አመክንዮዊ ትውልድን የመፍጠር መስመር መከተል ከእያንዳዳችን በግል፤ ከሁላችንም በጋራ የሚጠበቅ የመብት ግዴታችን ይመስለኛል። የግፍ #ሞት ይቁም!
 
ለተከበሩ ዶር ነገደ ጎበዜ ጓዶች፤ ቤተሰብ፤ ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን እመኛለሁኝ። ለዶር ነገደ ጎበዜም በስደት መኖር የሱባኤ ጊዜ ነውና አማኑኤል አባቴ ከፃድቃን ሰማዕታት ጋር ያድርግልን። አሜን።
 
እንዴት አደራችሁልኝ። 
 
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
14/11/026.
ነፍስ ይማር። አሜን።
 
ዶ/ር ነገደ ጎበዜ አረፉ
"ለበርካታ አስርት ዓመታት ቤልጂየም ብራስልስ በስደት የኖሩት የሜኢሶኑ ከፍተኛ አመራር ነገደ ጎበዜ (ዶ/ር) ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።
 
“ሕገ መንግሥት ምርጫና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ - ትላንት ዛሬ እና ነገ” የምትል በ1997 ያሳተሟት መፅሐፍ እነ በረከት ስምኦንን ጭምር ፀጉር ያስነጨች ነበረች። 
 
እሳቸውም በወቅቱ በተፈጠረው የተሻለ የፖለቲካ ምህዳር ምክንያት ወደ ሀገር ቤት ለመግባት ሞክረው ከቦሌ መመለሳቸው ሲነገር ነበር።
እንዲሁም "ይድረስ ለግንቦት ከየካቲት" የተሰኙ መፅሐፍት ደራሲ ናቸው።
 
የሚል አነጋጋሪ መጽሐፍ ያሳተሙትና የመኢሶን ከፍተኛ አመራር አባል የነበሩት ዶ/ር ነገደ ጎበዜ ከ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።
 
- ከታህሣስ 1959 ዓም – 1960 ዓም ድረስ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ሊቀ መንበር
- ከነሃሴ 1960- 1963 በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር የመጽሄት አዘጋጅ ቦርድ አባልና በ1963 የቦርዱ ሊቀመንበር
- ከነሃሴ 1962 – 1963 በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ፕሬዜዳንት
- በነሃሴ 1960 የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) መስራች አባል በመሆን ሰርተዋል።
ነፍስ ይማር"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።