#እግዚአብሄርም #ሲከፋው ያለቅሳል።

 

"ጥል ባለበት ዘንድ እርድ ከሞላበት
ቤት በጸጥታ ደረቅ ቁራሽ ይሻላል።"
 
 
• #እግዚዮ! አልኩ ማኽከነንም አከልኩኝ።
• #ውጡልን የተባለ፤ የተፈናቀለን ሕዝብ ጉዞውን እየተከተሉ በድሮን? ፍራቻው ምን ይሆን?
• እራሱን #እየጨረሰ ያለ መንፈስ።
• እራሱን #እየቆረጣጠመ ያለ ራዕይ።
 
የድሮን ጥቃት በኢትዮጵያ #ከሰለጠነ ዓመታት ተቆጠሩ። ድሮን ብረት ነው። ድሮን ማሽን ነው። የድንቢጥ ወፍ ያህል አንጎል ድሮን የለውም። የሚላክበትን ጸረ - ሰው፤ ጸረ - ተፈጥሮ ተልዕኮ በግዴለሽነት፤ በአረመኔነት የሚፈጽም የማያስብ፤ የማይሰማ፤ የማያለማ መከራ ነው። 
 
ድሮን ዕንባን ጭኖ ይሄዳል- ዕንባን ዘርቶ - ዕንባ ኮትኩቶ --- ዕንባን አስብሎ ግዳጁን ይወጣል። ስኬቱ የኢትዮጵያን #ሰቆቃ #በሰቀቀን ማወራረድ ነው። ያንተያለህ ነው። ለዛውም ለከፋው መጠጊያ ፍለጋ ክልትምትም ለሚል #የራስ ህዝብ።
 
ስለሆነም ሰው ጨራሽ፤ ተፈጥሮ #አምታሪ አምካኝ በሆነው የብረት በቀል ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ በዚህ የመከራ ማዕበል ውስጥ #እየተሰቃዩ ይገኛሉ። ህዝባችንም በፍርሃት ቆፈን ተውጧል። ግራ ቀኙ ተፋላሚ ኃይሎች ድሮን አላቸው። 
 
ድሮን የጀግንነት ጉዳይ አይደለም። የማሽን ስልጣኔ በሰው ልጅ ግብር ለአንዱ እርካታ ለሌላው የመከራ ናዳ--- የዕንባ ሱናሜ ----የተስፋ ማጣት ክምር፤ የትውልድ #ምንጠራ ነው። 
 
ማን ይሁን ማን የሚፈጽመውን የጭካኔው ልክ መተመን አይቻልም። ድሮን በካፒቴን አይመራም እና። ባለፈው ጃዋሪዝም "ድሮን ኦፕሬተር ውስጥ ቄሮ እንዳሉበት" ጠቁሞ ነበር። ቄሮ የአዲሱ ትውልድ አባል ነው። ጃዋሪዝም ያለው ከሆነ፤ የተባለው ነገር ቄሮወች ለራሳቸው ትውልድ #መከታ የተስፋ መጠለያ ቢሆኑ ምርጫዬ ነው። እኛ ባለፍንበት ትርምስ አዲሱ ትውልድ ባይደግመው ምርጫዬ ነው። 
 
የሆነ ሆኖ ወዳጅ ጠላት በሚል አራራቂ፤ #አፈራራቂ ቂም አዘል ኩነት የሰው ምታሮ በዘመን ሮሮ ይወራረዳል። በዚህ ሂደት አላሃችን፤ አምላካችንም #ያለቅሳል። ለቅሶ ምርቃትን #ያስነሳል።
 
በዚህ ሂደት አቤቱ ብልፄው እራሱን እየጨረሰ፤ እራሱን #መለመላ እያስቀረ እየቆረጠመም ይገኛል። "ውጡልን የተባሉ፤" የፈሩ ራሱን የመረጠውን ህዝብ መንገድ ላይ ጠብቆ ይሁን፤ ተከታትሎ ዕንባን ማሳቀፍ የትኛው ቃል ይመጥንልኝ ይሆን? ለቀብር እንኳን በፍራቻ ከተገኜው ቦታ እንደ ተፈጸመ ነዋሪወች ይገልፃሉ።
 
ሌላው ሚዲያወች እባካችሁ #ጥንቃቄ አድርጉ ዛሬ ፋኖ በሁሉም ቦታ አለ "ቢዛሞ" ሞታችን ይክሳል፤ መሰል አገላለጽ እናንተ ምቹ ሁኔታ ተቀምጣችሁ ይህን መሰል ድርብ መከራ ያመጣል። ቀያቸውን ለቀው፤ ንብርታቸውን ተዘርፈው፤ ህይወታቸውን ለማትረፍ የሚያደርጉት ጉዞ በዚህ ዋይታ #ተጠናቀቀ። 
 
ጎጃም ቢሄዱ ምን ያመጣሉ ተብሎ ይሆን??? ስሌቱ አልገባኝ አለ። 
 
#እርገት ይሁን።
 
የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች እባካችሁ በትህትና፤ በአክብሮት ልለምናችሁ፤ ከዚህ ምስቅልቅል #ሰቆቃዋ #ኢትዮጵያ #ትወጣ ዘንድ ጸልዩላት። እባካችሁ? ምን ያደርግላታል ለኢትዮጵያ #ፖለቲካ???? ማለቂያዋ ዕንባ እና የሰው ሞት የለት ተለት መርዶ።
 
መከራ ውስጥ ላላችሁ ወገኖቼ ሁሉ እግዚአብሄር #ያጽናናችሁ። አሜን።
የBBC ፎቶ አልተጠቀምኩም። አረመኔውን ድሮን ቤቴ ውስጥ ማየት አልፈቀድኩም።
 
የሃዘን ዳርቻም ፈጣሪ አምላክ ያድርገው። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ደህና እደሩልኝም። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ።
Sergute©Selassie.
12/11/026.
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
()()()()()//////()()()()()()()/////()()()()
#BBC.
BBC «በኦሮሚያ ክልል ኪረሙ ወረዳ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን እማኞች ተናገሩ»
«በኦሮሚያ ክልል፣ ኪረሙ ወረዳ ባለፈው ሳምንት በተፈፀመ የድሮን ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተጎጂ ቤተሰብ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።»
 
«ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት እማኞች እንዳሉት በአዲሱ አደረጃጀት በምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ውስጥ በተካተተው በቀድሞው ምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ኪረሙ ወረዳ ባለፈው ሳምንት ዓርብ፣ ጥቅምት 27/ 2019 ዓ.ም. በተፈፀመው ጥቃት ሕፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ 36 ሰዎች ተገድለዋል።»
 
«የጥቃቱ ሰላባዎች በጊዳ አያና ወረዳ ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ለደኅንነታቸው ሰግተው ከአካባቢው ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል በመጓዝ ላይ የነበሩ ሲቪሎች መሆናቸውን እማኞቹ ተናግረዋል።»
 
«ቢቢሲ ከኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት እንዲሁም ከመከላከያ ሠራዊት ስለጥቃቱ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።»
«ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ተፈናቃዮቹ በቁጥር ሕፃናት እና አረጋውያንን ጨምሮ ከ200 እስከ 300 የሚገመቱ ናቸው።»
ለወትሮው መረጋጋት በራቀው የክልሉ አካባቢ በሚፈፀሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች የሚፈናቀሉ ነዋሪዎች በርካታ ናቸው።
 
የአርብ ዕለቱ የድሮን ጥቃት የተፈፀመውም የሚኖሩበትን ቀዬ ለቅቀው በመውጣት የገጠር መንደሮችን በእግራቸው እያቆራረጡ ሲጓዙ በነበሩ ተፈናቃዮች ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
 
"ምሽት ላይ በባትሪ ብርሃን እየታገዝን በምንጓዝበት ወቅት ድሮን ሲያንዣብብ ተመለከትን። እባካችሁ ባትሪውን አጥፉ" እያልን ስንመክር" ድሮኗ ድንገት መተኮሷን በመግለጽ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ነዋሪ የተፈጠረውን አስረድተዋል።
 
ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ ከጠየቁት የቢቢሲ ምንጮች ሌላኛው፣ ጥቃቱ የተፈፀመው ወዴሳ ዲማ የምትባል ቦታ ላይ ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት መሆኑን ጠቅሶ፣ የድሮን ጥቃቱ ሁለት ጊዜ መፈፀሙን ተናግሯል።
 
"የደረሰው ጉዳት ከበድ ያለ ነው። ሰው መሆን የሚያስጠላበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው። በገዳ ኮማንዶ ምክንያት ተፈናቅለው ጉዞ ላይ እያሉ ዓርብ በ27 ነው ጥቃቱ የተፈፀመው። ቢያንስ 36 ሰዎች ይሆናሉ የሞቱት። የታዘሉ ሕፃናትም ይገኙበታል" ብለዋል።
 
በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል ስምንቱ ሕፃናት፣ አምስት ነፍሰጡር ሴቶችን ጨምሮ 17 እናቶች፣ ሦስት ዓይነ ስውራን መነኩሴዎች እና ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሦስት ሽማግሌዎች እንደሚገኙበት እማኙ ጠቅሰዋል።
 
"ማንነታቸውን መለየት የማይቻል ሰዎችም አሉ" ብለዋል።
 
ቢቢሲ ተፈፀመ ስለተባለው ጥቃት እና ስለደረሰው ጉዳት ከገለልተኛ ወገን አላረጋገጠም።
በወለጋ የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየተባባሱ ሲሄዱ የጥቃቱ ዋነኛ ተጎጂዎች ደግሞ ንጹኃን ነዋሪዎች እየሆኑ መጥተዋል።
 
በምዕራብ ኦሮሚያ ዞን በአቤ ዶንጎሮ፣ ኪረሙ እና ጊዳ አያና ወረዳዎች በርካታ የታጠቁ ኃይሎች የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ተቀናቃኝ የታጠቁ ቡድኖች፣ በአካባቢው የተደራጁ ሚሊሻዎች እና ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ኃይሎች ይገኙበታል።
 
ከ2011ዓ.ም. ጀምሮ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚያደርገው ግጭት የምዕራብ ኦሮሚያ የጸጥታ ችግር ዋነኛ መንስኤ ሆኖ ቆይቷል። 
 
የፌዴራል እና የክልል ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ሸኔ በሚል ስያሜ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድን ለማዳከም እና እንቅስቃሴውን ለማስቆም ወታደራዊ ዘመቻዎች ያካሄዳሉ።
 
ሆኖም ግን በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ጨምሮ ሌሎች የታጠቁ ኃይሎች በአካባቢው መኖራቸው የጸጥታውን ችግር ይበልጥ አወሳስቦታል።
 
በአርብ ዕለቱ ጥቃት ከተገደሉት መካከል አራቱ የቅርብ ዘመዶቻቸው መሆናቸውን የተናገሩ የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ፣ ጥቃቱ በተፈፀመ ማግስት ጉዳት ደርሶባቸው የተረፉ አራት የወንድማቸውን ቤተሰቦች ይዘው ወደ ሕክምና መሄዳቸውን ገልፀው፣ ሟቾቹ ከ30 በላይ መሆናቸውን እንደሰሙ ተናግረዋል።
 
"በአጠቃላይ ንፁኃን ናቸው የተገደሉት፣ የገዳ ኮማንዶን ጥቃት ሸሽተው ወደ አገር ቤት በእግራቸው ሲጓዙ የነበሩ ናቸው። በንጹኃን እመጫቶች እና ሕፃናት ላይ ነው ይህ የተደረገው" ሲሉም የደረሰውን ጉዳት አስከፊነት አስረድተዋል።
 
በጥቃቱ ስምንት የቤተሰብ አባላቸውን እንዳጡ የተናገሩት እኝህ ተጎጂ፣ "ወንድሜ ከሁለት ልጆቹ እና ባለቤቱ ጋር ተገድለዋል። ሌሎች አራት ቁስለኞችን ደግሞ እያስታመምኩ ነው" ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል።
 
የቤተሰብ አባሎቻቸው እርሳቸው በሚኖሩበት ወዴሳ ዲማ ጎጥ በኩል ሲያልፉ ሸኝተዋቸው እንደተመለሱ ከዚያ ግን መሣሪያ ሲጮህ መስማታቸውን ነዋሪው ያስታውሳሉ። 
 
"ከዚያ ስልክ ተደውሎልኝ ወደ ሥፍራው ስሄድ እንዳይሆኑ ሆነው አገኘኋቸው" ይላሉ።
ቁስለኞቹ በቂ ሕክምና እንዳላገኙ የሚናገሩት ግለሰቡ፣ የእርሳቸውን ቤተሰቦች ጨምሮ በጥቃቱ የተጎዱ 16 ሰዎች መመልከታቸውን ተናግረዋል።
 
ሌላ የዓይን እማኝም በኪረሙ በኩል አድርገው ወደ አማራ ክልል ጎጃም ለመሻገር እየሄዱ ሳለ ጥቃቱ መፈፀሙን ተናግረዋል።
እማኙ እንደሚሉት ተፈናቃዮቹ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ባደረባቸው ስጋት ምክንያት አካባቢውን ለቀው ለመውጣት በጉዞ ላይ ነበሩ።
 
"የሚያሳዝን ነው። የተገደሉትን ዝም ብለን ጫካ ውስጥ ነው ቆፍረን የቀበርናቸው፤ እንዲያው እንደ አውሬ ነው የተጣሉት። በጣም የሚያሳዝን ነው። ጠዋት ነው አስከሬን አንስተን በጅምላ የቀበርነው። ሕዝቡም ተደናግጦ ስለነበር ይዞ ለመሔድም አልተቻለም፤ ቤተክርስቲያን ለመሄድም ፈራን" ብለዋል።
 
ከጥቃቱ በእናቶቻቸው ታዝለው የነበሩ ሁለት ሕፃናት በተዓምር መትረፋቸውንም ነዋሪው ገልጸዋል። አንዷ ሕፃን እግሯ ላይ ጉዳት ቢያጋጥማትም ከሞት መትረፏን እና አንድ ወንድ ሕፃንም ከሟቾቹ መካከል በሕይወት መገኘቱን አብራርተዋል።
 
ሌላ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪም በጥቃቱ የተገደሉ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ስምንት ሕፃናትን ጨምሮ የ36 ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት መፈፀማቸውን ገልጸዋል።
 
"ከአሊ፣ ከዋጃ እንዲሁም መለከታ አንዶዴ ከሚባሉ ከጊዳ አያና ወረዳ የተለያየ ቦታ ተፈናቅለው እየሄዱ እንደሆነ ነው ሲነግሩን የነበሩት። እኛ ካለንበት ቀበሌ ሲደርሱ ስንቅ ለሌላቸው ስንቅ እየሰጠን ለደከሙትም እያሳደርን ነው የምንሸኛቸው። መንገድ ላይ እያሉ ነው ጥቃቱ የተፈፀመባቸው" ብለዋል።
 
የሞቱትን እዚያው ጥቃቱ በተፈፀመበት ወዴሳ ዲማ ቀበሌ በጅምላ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው እንደተፈፀመ የሚናገሩት ነዋሪው፣ "ወደ ቤተክርስቲያን ለመውሰድ ከተሰባሰብን ልንመታ እንችላለን ብለን ስለፈራን ሰብስበን ቀበርናቸው" ሲሉ አስረድተዋል።
 
ከጥቃቱ በኋላ ሌላው ማኅበረሰብም በስጋት እየተፈናቀለ መሆኑን ነዋሪው አክለዋል።
"ጥቃቱ ከተፈፀመ በኋላም ትናንት ምሽት ድሮን ሲቃኝ ነበር በድጋሚ አልወረወረም እንጂ። አሁንም ቅኝት ያደርጋል" ብለዋል።
በቅርቡ በምዕራብ ኦሮሚያ በኪራሙ፣ አቤ ዶንጎሮ እና ጊዳ አያና ወረዳዎች የፋኖ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ቁጥራቸው ያልተገለጸ ሰዎች መሞታቸውንና በርካቶች መፈናቀላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ኦሮምኛ ተናግረዋል።
 
ነዋሪዎቹ በጥቃቱ በርካታ እንስሳት እና ንብረቶች ተዘርፈዋል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ በሦስት ወረዳዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መፈጸማቸውን አረጋግጠዋል።
 
አቶ ኃይሉ ጥቃቱን ስለፈጸሙት ታጣቂዎች ሲናገሩ "አማርኛ ተናጋሪው ሸኔ እና ኦሮምኛ ተናጋሪው ሸኔ" በጥቃቶቹ ላይ ተባባሪ ናቸው ሲሉ ከስሰዋል።
 
መንግሥት ጥቃቶቹ በሚፈጸሙባቸው ወረዳዎች ውስጥ ባሉ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑንም ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት አርብ ስለተፈጸመው የድሮን ጥቃት ከመከላከያ ሠራዊት እና ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሚኒኬሽን ምላሽ ለማግኘት ቢቢሲ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
 
የመከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቃል አቀባዮች ለቢቢሲ የስልክ ጥሪ እና የጽሑፍ ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።
የአካባቢው ነዋሪዎች 'ገዳ ኮማንዶ' የተባለ የክልሉ መንግሥት ኃይል በአካባቢው ጥቃት እንደሚፈፅም ቢገልፁም፣ የክልሉ መንግሥት ግን ገዳ ኮማንዶ በሚል ስም የተደራጀ ኃይል አለ መባሉን አይቀበልም።
 
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት የሰላምና ደኅንነት ዘርፍ አማካሪ የሆኑት ጄኔራል ኃይሉ ጎንፋ በቅርቡ ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት፣ "ገዳ ኮማንዶ የሚባል አደረጃጀት የለንም" ማለታቸው ይታወሳል።"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።