ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል።

 

ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል።
 
ይበቃኛልን የተማርኩት ከቅዱሱ፣ ከሰማዕቱ፣ ከድንግሉ ከመምሩ፣ ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነው። ቅዱሱ አባታችን ወደ ቈላስያስ በላከው መልዕከቱ ምዕራፍ 4 ቁጥር 10 እስከ 12 „ ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ ልታስቡ፡ ስለ ጀመራችሁ በጌታ እጅግ ደስ አለኝ። ጊዜ አጥታችሁ እንጂ ማሰብ ታስቡ ነበር። ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ፡ መብዛትንም አውቃለሁ። በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬያለሁ። ሃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ።“ 
 

 
 
ይህ የኑሮዬ ት/ቤት ነው። ስለሆነም ቆሜ መኖር ቻልኩ። በማልችለው መጠራቅቅ ውስጥ ግን አለሁ። ልሻገረው በማልችለው ሙላት አሁንም አለሁ። አቅመ ቢስ ሆኜ እንኩቶ ሲፈትለኝ ግን አለሁ። መኖሬ ቀዳዳ የተሰወረበት ቢሆንም ግን አለሁ። የተሰጠኝ ይህ ብቻ ስለመሆኑ ስለማወቅ ሳልንጠራራ ልኬን አውቄ አንድዬን አመስግኜ ኑሬዬን ዝቅ ብዬ አክብሬ እንዲያውም አንደላቅቄው እኖራለሁ።
ከሁሉ በላይ ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል። እባብ እንጉቻችሪት ጊንጥ እስስት ሆኜ አልተፈጠርኩም። ሰው ሆኜ በአምሳሉ እንደፈጣራቸው ሁሉ ተስተካክዬ ነው። ስለዚህ እማስበው እምኖረው - እምራማደው - እምሄደው እንደ ሰው ነው። 
 
እንደ ሰው ለሚያስብ ደግሞ ቀለም - እውቀት - ዘር - ደረጃ ቦታ - ከፍ ዝቅ - ሁሉም እኩል በመስመር ገብተው እንደ ሰው ይታያሉ። ለእኔ ሰው የሆነ ሁሉ ለእኔ ተጨማሪ ኃይልና ዕሴት ፈጣሪ አቅሜ ጌጤ ግብሬና ሽልማቴ ነው። 
 
በሰው ልጅ ተፈጥሮ እስከ አላላገጠ ድረስ። ስለመኖርባት ዓለም ትርጉም መነሻው ሰውነት ብቻ ነው። ሰዎች በሰሩት በፈጠሩት - በተቃኙት - ባደራጁት - በሞቱለት በደሙለት - ዓለም ሰላም አግኝቼ እኖራለሁ። ስለዚህ በሰወች መሃከል ስለምን ልዩነት አደርጋለሁ?
 
ሰው ከሰውነት መደቡ ዝቅ ብሎ በመንጋው ሲያስብ ያ ከፍጥረቴ ነገሬ ጋር የተለዬ ስለሆነ ዓይኔ ሆነ መንፈሴ፤ ሩሄም ይጸዬፋዋል ከምል ጎልቶ የማይታይ የነፈሰበት እርቃን ብቻ ይታኛል። ተዚህ ሀገር አሻንጉሊቶችን ልብስ አልብሰው ማሻሻጫ አድርገዋቸዋል። ወይንም ከጎማ የተሠራውን ሰው አግብተው ዬሚኖሩም አሉ። እንደዛ ነው የማያቸው። 
 
ህሊናቸው መንፈሳቸው ልዝ ስለሆነ ጢስ ብቻ ነው የሚታዬኝ ውስጣቸው፤ ጢሱ ደግሞ መርዝ ነው። መርዙ ደግሞ የሰው ዘርን የሚያጣፋ የሚያቃጥል ብቻ ሳይሆን ሰውን ከሰው አለያይቶ ምድርን ምደረበዳ ለማደረግ የሚደረግ ዘመቻ በመሆኑ ጠላት ነው - ለእኔ። ከሁሉ በላይ የፈጣሪ አምላኬ ሥነ አምላካዊ ተፈጥሮንም የሚዳፈር ስለሆነ አብዝቼ እጸዬፈዋለሁ። ይከረፋኛልም።
 
ሰለሆነም ለእኔ ከዚህ በላይም በታችም ሳልወርድ ሰው መሆኔ ብቻ በቂ ነው። እዬገረመኝ - ሰረሰረኝ። እዬሰረሰረኝ በረበረኝ። እዬበረበረኝ - አወቀኝ። እኔኑ መሰጠኝ ሰው መሆኔን ብቻ ተረጎመልኝ። ሰው መሆኔን ብቻ አነበብልኝ። ሰው መሆኔን ብቻ አመሳጠረልኝ። 
 
ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል!
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ አሜን። 
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
20.12.2025
መኖራችን ካንፓሳችን፤ ኮንፓሳችንም።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።