#የተከለከለ ~~--- ፍቅር።
ከሥርጉተ ሥላሴ 03.10.2013
#ፍቅር ምንድን ነው?
ፍቅር ፍውሰት ነው - ድህነት!
ፍቅር ጣዕም ነው ንጥረ- መረቅ!
ፍቅር ክብረት ነው የከበረ - የሚያስከብር።
ፍቅር ኃብታም ነው ዲታ።
ፍቅር ምህረት ነው ሰላም!
ፍቅር ወድ ነው ስጦታ።
ፍቅር ጻድቅ ነው የመስቀል ወተት።
ፍቅር መስዋዕትነት ነው ጤና አዳም።
ፍቅርን ሲሰጡ ሊፈቀሩ የሚችሉ ፍጡራን ፍቅርን ሲከለከሉ ደግሞ ማመጻቸው አይቀሬ ነው።
እናት ከሁሉም በላይ ትውደዳለች።
እናት የመጀመሪያዋ የህይወት #ትምህርት ቤት ናት።
እናት መቅድመ የቤተሰብ አሰተዳደሪ የተፈጥሮ ሙሁራ #ሊቀ-ሊቃውንት ናት።
እናት የርህርህና #መግቢያም አውራም ናት።
ሴት እህት ስትሆን ትፈቀራለች።
ሴት አክት ስትሆን ትጠጋላች።
ሴት ሚስት ስትሆን እንደ ነፍስ ትታያለች።
ሴት ጓደኛ ስትሆን ትታመናለች።
ሴት እናት ስትሆን የጸጋ ስግደት ይሰገድላታል።
እኔ እንደማስበው በእምነቴ በኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አምስቱ #አዕማደ ሚስጢራት ላይ የእናታችን የቅድስት ድንግልና ማርያም ልዑቅ ነገረ ሳይደመር መቅረቱ በጣም ይጎረብጠኛል።
እንደሚገባኝ ግን የተዋህዶ ልጆች ለቅድስት እናታቸው ለድንግል ማርያም ያለን ልዩ ፍቅርና ስስት የአምልኮ ስግደት ይገባታል ብለን እንዳንሞግት ብልሆቹ አበው አስበውበት፤ ምንአልባትም መንፈስ ቅዱስም አቀብሏቸው ወይንም ሚስጢር ገልጦላቸው ሊሆን ይችላል። ለማንኛውም በጋህዱ ዓለም ስሌት ስንመጣ … በፖለቲካ አስተሳሰብ ሴት ላቅ ስትል ግን „#ጉልበታምንት“ ይለጠፍላታል። #ኃይለኛ ትባላለች። #የተከለከለ ፍቅር ይሏችኋል ይህ ነው።
ሴት ገረድ ስተሆን ትወደዳላች።
ሴት ሎሌ ስቶሆን ትደነቃለች።
ሴት የቤት ውስጥ ሰራተኛ ስትሆን ስንዱ ትባላለች።
ሴት ስታጎርስ የራህብ ደራሽ ትባላለች።
ሴት ጓዳ ጉድ … ጉድ ስትል ዓይን አብሮ ይዞራል
መንፈስም አብሮ ይንከራተታል። ስሜትም አብሮ ይከትማል።
ሴት እንግዳ ስታስተናግድ ትመሰገናላች።
ሴት ልጅ ስትሰጥ በዓይኔ ላይ ፍሰሺ ትባላላች።
ሴት ስልጣን ልትጋራ ብቅ ስትል ግን „#ኃይለኛ“ ተብላ ትኮረኮማለች ወይንም ትባረራለች።
ሌላ ድልዝ ይፈልግላታል። ሌላ ልጥፍ ይፈለግላታል። ሌላ የሰብዕናዋ ድክምት ቁፋሮ ይጀመራል። #የተከለከለ ፍቅር …
ሴት ገንዘብ ያዥ ስትሆን ትመረጣለች።
ሴት ገንዘብ ስትሰበስብ ታማኝነቷ የሰበክላታል።
ሴት አዳራሽ ስታሰናዳ ትሞካሻለች።
ሴት ስታነጥፍ ወይንም ስትነጠፍ እንደ ብርቅ ትታያለች።
ሴት ቅራኔ ውስጥ ገብታ ስተቀረቀር ይጨበጨብላታል።
ሴት መድረክ ላይ ወጥታ አቅም ባላው ብቃት እኩል ስተመጥን ግን በግሳፄ ትባረራለች …..
ሴት ስትለብስ ትፈቀራለች።
ሴት ስተሸቀረቀር ይዜምላታል።
ሴት የተፈጥሮን ፍቅር ስተመግብ #ንቢት ተብላ ትሞገሳለች ትመገባለች።
ሴት ሽክ ብላ ከጎን ስትጓዝና ግብዣ ላይ እኩል ስትቀመጥ #አጃችን ይሞላል።
ሴት ገብያ ወጥታ ቀጨር መጨሬውን ስትሸማምት አበጀሽ ትባላለች።
ሴት ኮስሜቲክ ስተገዛዛ ጎሽ ትባላለች፤ ሴት #ወንበርን ልትጋራ፤ የፖለቲካ ውክልና ስትጠይቅ በብቃቷ ልክ፤ ጥንካሬዋን ስታስመከር ግን ትገፈተራለች …. ቆመጥ ይዘጋጅላታል ….. የተከለከለ ፍቅር ….
ሴት ቤት ስትውል እንደ እመቤት ትታያለች።
ሴት አንገቷን ደፍታ መከራን ስትቀበል ትወደሳላች።
ሴት የልጆች አሳዳጊ ብቻ ስተሆን ትበረታታላች።
ሴት በማይታዩ ሩትን ተግባራት ስትሰማራ ማን እንዳንቺ ትባላለች።
ሴት አንደበቷ ታስሮ የሳሎን ጌጥ ስትሆን ማለፊያ ይባልላታል።
ሴት ግን የመንግሥትን ቁልፍ ኃላፊነትን እኩል ለመጋራት ብቅ ስትል #ጦርነት ይታዋጅባታል። የተከለከለ ፍቅር ….
ሴት ስትጋግር … ስትሰራ …. ስታጥብ … ልብስ ስትተኩስ፤ ስታረግዝ …. ስታጠባ …. ከሚፈለገው ቦታ ላይ ተገኝታለችና ይዘፈንላታል። ከዚህ አለፍ ብላ የመብትና የእኩልነት ጥያቄ ስታነሳ ግን ትወረወራላች …. እውነት ለመናገር በዘመናችን ያሉ ሴቶች እንኳን ጥበቃና እንክብካቤ ሊያገኙ ቀርቶ ገፍተው የሚወጡት እንኳን #ለምነው ለመታገል እንኳን ፈቃድ አያገኙም በወንድ ትምክህተኞች ….
ዛሬም ከዛሬ 100 ዓመት በፊት ካላው ኮረብታ ላይ እንዳሉ አሉ እነ ተባዕት …. ይህን በስማ በለው ሳይሆን እኔ በህይወቴ ከተሰደድኩ በኋላ ያዬሁት ነው። #ምስክርም ነኝ። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከገበርዲን እና ከከረባት ያልወጣ ስለሆነ የኢትዮጵያ እናቶችን ዕንባ ለማቆም ረጅም ጊዜ ይጠይቃል በሚል፤ የትግሌ ማዕከል አድርጌ የታገልኩት።
በፍጹም ሁኔታ የነፃነት ትግሉ ሆነ ነገ የሚታሰበው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሰረቱና እርገቱ ከሴቶች ውጪ ሊታሰብም ሊሳካም እንደማይችል በጣም በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። የነፃነት ትግሉ የሴቶችን ሙሉ ተዋፆ በአጽህንኦት፤ በተደሞና በአርምሞ ይጠይቃል።
ይህቺ ለመላሾ አሉ …. የሚሏት ልጥፍ ሽፋን ለማንም አይበጅ ነገንም አያበጅ። ዶማ …. መንገድ ነው። የነፃነት ትግሉ ሙሎዑነት ሊረጋገጥ የሚችለው የሴቶችን የመጠነ ተሳትፎ ተግባር ላይ ሲያውል ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ ሀገራችን ካላት ያልተነካ ቅምጥ ኃይል በላይ የሴቶች ሃብት እስከ ዛሬ ድረስ ሥራ ላይ አልዋለም … ነገም ጠንዝሎ ይታዬኛል። እርግጥ ማሳሳቻ አስፓልት አለ። የሴቶች መምሪያ ከፍተናል … ጉዳያቸውን የሚከታተል መዋቅር ዘርግተናል … ይህ ሴቶችን ብቃት የሚየቀጭጭ አፋኝ የማስመሰያ ጅራፍ ነው።
አውሮፓ ያላችሁ ሁሉ እንደምትከታተሉት አውሮፓ በ ኢኮኖሚ ውጣ ውረድ ተሰቅዞ ሲባትልና ሲብተለተል የመፍትሄው ጭንቅላት የተገኘው ከጀርመን ነበር። የጀርመኗ መሪ ጠ/ሚ አንጅላ ሜርክል ቀጥ አድርገው በማያዝ ማገር ሆነው አውሮፓን ከውርዴት ዘመኑንም ከጥፋት ታድገውታል። ጠ/ሚር ሜርክል ፓን አውሮፓኒስት ናቸው።
በተግባር የከበሩ የመጀመሪያዋ የጀርመን ሴት መሪ። የ እንግሊዟ ታችር፤ ንግስት ኤልሳቢጥም በ አጭሩ ተፍርተው በ አጭሩ ተቀጩ እንጂ ልዕልት ደያናም አሳይተዋል አስመስክረዋል … ያን ጉልበታም ተዝቆ ማያለቅ ብቃት ….
በዘመነ ክሊንተን ያን ስሜትን የሳበ የፕ/ ቢል ክሊንተን ቅብጠት ብልኋ ባለቤታቸው እመቤት ሄነሪ ክሊንተን የሆነውን እንዳልሆነ አድርገው ትቢያ አልበሰውታል። በወቅቱ አንድ ጋዜጠኛ እንዲህ ሲል ጠይቋቸው ነበር … የሚባለውን አልሰማሽንም … አላነበብሽውንም ሲል“ ብልኋ እመቤት ግን „ እነቴ ከልጅነቴ ያስተማረችኝ ሰው የሚለኝን ከሰማሁ የምሰራው የሰውችን እንጂ የ እኔን እንዳልሆን ነግራኛለች፤ አስተምራናለች። መርሄ ይህ ነው እኔ የኔን ሥራ እሰራለሁ ሌሎች ደግሞ የራሳቸውን ይሰሩ“ ነበር ያሉት ሰማዬ ሰማዬት የዘለቅ ዕጹብ መልስ ነበር።
ከዚህም በኋላ በዘመነ ፕ/ባራክ ኦባማ የውጭ ጉዳይ ሚር/ ሆነው እጅግ ውስብሰብ ፈታኝ በሆኑ መሰናክሎች ሁሉ በማለፍ የሰቴችን የመወስን አቅም በተግባር አሳብበውታል። አሁንም የፕ/ ባራክ ኦባማ ባለቤት ቀዳማይ እመቤት ሚሻዬል ኦባማ ሁለገብ ንብ በመሆን ባለቤታቸውን ለሁለተኛ ጊዜ የሥልጣን ባለቤት አብቅተዋል … ዓይን ካላችሁ ከዚህ ሀቅ ጋር ታረቁ …
በ አፍሪካ ታሪክ ጉልበታሙ የፕ/ ማንዴላ ተገዳሎ የምዕተ ዓመቱ ታላቅ መዘክር ነው። በፆታዊ ችግር የተፈጠረውን ነገር ዝለሉትና ወ/ሮ ዊኒ ማንዴላ ባላቤታቸው እስር ቤት በነበሩበት ጊዜ የነፃነት ትግሉን በግንባር በመምራት፤ ልጆቻቸውን በማሳደግ፤ ለትዳር አጋራቸው አጥር ቅጥር በመሆን የክንድ ክንድ ነበሩ። ይህን ከባለቤታቸው ጋር ይጻጻፉ የነበሩትን የነፃነት ትግል ትምህርት ቤት ከነበረው ዝክረ ደብዳቤዎች ማገናዘብ ይቻላል።
በ እኛዋ አፍሪካ … በቀደመው ዘመን ንግስት ዘውዲቱ የመቻልን ተፈጥሮ፤ ከእቴጌ ምንትዋብ የተግባር አርበኝነትን፤ ከ ከዕቴጌ ጠይቱ የብልህነት የፖለቲካ መሪነትን ጠበብትነትን ጠብተን አድገናል። በዘመችንም … እነሳራ ግዛው፤ እነ አያልነሽ፤ እነሽብሬ፤ እነብርቱካን ሜዲቄሳ እነሰርካለምን እነርዕዮትን እነ በላይነሽን ስንቶቹን የነፃነት አርበኞች እናት ሀገራችን አፍርታለች። መሬታች መሃን አይደለም። ተሳትፎውን ያነጠፈው ትምክተኝነት ብቻ ነው።
በ አጽህኖት እናገራለሁ የፖለቲካ መሪዎቻችን የውስጥ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል። በፍጥነት። እንዲሁም በዬአጋጣሚው የሚሾሟቸው የበታች ገዢዎቻቸውንም ለውጡ ገፍቶ እንዲያነጥራቸው እንሻለን። ጣላቆቹ የጉሮሮ አጥንቶች እነሱ ናቸውና። ፓለቲካ አመራር ልም ነው። እኔ የማዬው ግን ሽርክትና ግርድፍ ሆኖ ነው። አብሶ አጋርን በመገፍተር እረገድ ከንፍሮ የወጣ አንድም መሪ አልገጠመኝም። ቆሞ ስለ አርበኛ አንስት የሚመሰክር፤ የፖለቲካ መሪዎቻችን፤
እርግጥ ነው ሥር ላይ ያለው ተግባርን የሚያደምጡት ከበታቾቻቸው ለዛውም ስታስቲክሱን በሩቁ ነው። ወረድ ይበሉ። ሰፊ መድረክ ይክፈቱ። የትችት አንባ ይወጁ እንዲአድጉ እንዲመነደጉ ከፈለጉ … የበታቾቻቸው እኮ ስለፓርቲያቸው ማንፌስቶ ዲቤት ቢገጥማቸው ከተረት ተረት ያለፈ የማኒፌስቶውን ፋክት ይዞ ፋክትን በፋክት አፋጭቶና አታግሎ የነጠረውን የፓርቲያቸውን አቃም አሸናፊ ለማድረግ አቅም የለሾች ናቸው።
ያው ቁንጮቹ የሚሉትን በተገኘው አጋታሚ ሁሉ እንደ ፓፓጋይ ሲደግሙና ሲሰልሱ ዓመት ይዞ እስከ ዓመት ከዛው ለዛው ሲዳክሩ ነው የሚታዩት … እርግጥ ላይኞቹ ሴቶች ማለት ሲጀመሩ የታችኞች ቅጂውን እንደ ገደል ማሚቶ ያስተላለፉ ይሆናልና እባካችሁ ላይኖቹ ጀመሩት ….
ተከታታይ የሆነ አቅም ያለው የመንፈስ ጥሪት ለመገንባት ይሞክሩ ፖለቲከኞቻችን …. የሴቶችንም ነገረ ሚስጢር አክለው …. የሃይማኖት አባቶቻችን ሲያሰተምሩን ነገረ ማርያምን ነጥለው ሳይሆን አስቀድመው በፍቅራ ቅጥል እያሉ ነው። እኛም እንደነሱ ሆነን እናታችን የማናሰነካው አሳምረው ስለጠረቡን ነው።
ለነገሩ ሹሞቹም እኮ የፖለቲካ ድርጅታቸው ማንፌስቶ በቅጡ የማያውቁ ናቸው። ፈጽሞ አላመረበትም የትግሉ መስመር ድርቅ የመታው ነው። ጎድሎበታላ ታላቅ ነገር ቅናዊ ዕይታ፤ ሥልጣንን የማጋራት ግልጽነት፤ ኃላፊነትን በቅመም የመመጠን ትርጉም ያለው ተግባርና እርምጃ አሯል። አይታይም።
የመከነ ጉድ ነው …. በዬትኛውም ሁኔታ በቦታው የሌለ ነገር ሴቶችን በ አክብሮት እኩል ለማሳተፍ ያለው ፈቃደኝነት ልሙጥ ነው። ድረቅ የተጫወተበት፤ ዝናብ ሲሄድበት የከረመ አለት የመሰለ ለዛ የለሽ ዕሳቤ ነው። በጣም በረቂቅ ሁኔታ በሴቶች ላይ የተጣለው ማዕቀብ ዘመንና ጊዜ ኢፈታዋል የሚል ግምት የለኝም። የተሳሳረ ትብትብ ነገር ነው። በሩ ተቀርቀሯል። ጭላንጭል መተንፈሿ ቧንቧው የታነቀ ነው ….
ህየውት ካለ ሴቶች ኮረኮንች --- አመዳም --- ቡላ ---- የፋደሰ ---- ቀዝቃዛ --- የነፈዘ ----- ነው …. ትግሉም ዕጣ ፈንታው የተደረገው በዚህ መልኩ ነው። ይፍታህ በሉት! ነይልኝ --- ነይልኝ --- „የህይወቴ ህይወት“ ለዚህ ብቻ ፍቅር … ይፈለጋል። ትውልድን ለመገንባት፤ ታሪካዊ ድርሻን ለመወጣት ግን ለ አጃቢነት ብቻ። ወይንም ለዘበኝነት። ለሚመጥን የሥልጣን ክፍፍል ማነቆ እገዳ ክልከላ … ሰባራ ጉድ …. ጨምዳዳ ….. የተሸበሸበ …. ሽራፊ …. ያመለ … የሻገተ …
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
20.12.2025
መኖራችን ካንፓሳችን፤ ኮንፓሳችንም።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ