ለቀኑ ቀን ሲሰጠው የመፍትሄ #ቁልፍ ይገኛል እንዲህ፤ የተከበሩ ናሬንድራ ሙዲ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስተር እግዚአብሄር ይስጥልን።

 

• ለቀኑ ቀን ሲሰጠው የመፍትሄ #ቁልፍ ይገኛል እንዲህ፤ የተከበሩ ናሬንድራ ሙዲ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስተር እግዚአብሄር ይስጥልን።
• ዕለተ የኢትዮጵያ #ቀደምት የድንቅነት ታሪክ ብሩክ ቀን፤ ቅዱስ ቀን።
 
«የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር»
 
"አድርገህልኛል እና አመሰግንሃለሁ።"
 
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር @ethiopiannewsagency

ከኢትዮጵያ ህዝብ ባላነሰ በየሥርዓቱ ሲቀጠቀጥ፤ ሲቃጠል፤ ሲጨፈለቅ፤ ሲጨቆን፤ ሲገለል፤ እንደ #ደመኛ ሲታይ፤ ሲጠቀጠቅ፤ ሲያስፈልግ ሲዘረፍ፤ ሲያሻ በማቅ ሲጠቀለል፤ ሲያስፈልግ መላ ሁነቱ ለእግር ብረት ተዳርጎ #ግዞት ሲላክ፤ እንዲያም ሲል ሲታፈርበት፤ ሲያሰኛቸው አቃለው ሲያጣጥሉት ምን ከሌላው አገር የተለየ ታሪክ ኖሮ በሥርዓተ ትምህርት ሊካተት ይችላል ሲባል፤ ሲወረፍም፤ አንዳንድ ጊዜ ልበወልድ ታሪክ ጽፈው #ሲበቀሉት፤ ቀራንዮም ልከው ሲገርፋት፤ ሲሰቅሉት፤ ቀብረነዋል ብለው ሲሸልሉ፤ እንሆ ዛሬ ፈቃዱ ሆነ እና እራሱን አስከብሮ፤ እራሱን ገልጦ እንዲህ ቦግ ብሎ በራ የኢትዮጵንያዚም ታሪክ። 
 
የሚገርመው የኢህዲግ ቅሪት አካል፤ የብልጽግናም አዳዲስ ሹማምንቶች በተገኙበት ይህን የመሰለ የኢትዮጵያኒዝም ልብ አንጠልጣይ ሌሰን ሁሉም ቁጭ ብሎ ያደምጥ ዘንድ ለፈቀደ ልዑል እግዚአብሄር ምስጋናዬን አቀርባለሁኝ። ክቡር የህንዱ ጠቅላይ ሚር ናሬንድ ሙዲ #መንፈስ #ቅዱስ ነው ያናገራቸው ብየ አምናለሁኝ። እኛ እኮ አለን እንላለን እንጂ ውስጣችን ፈርሷል። እራሳችን እራሳችንን ፈቅደን እና ወደን እየናድነው ነው። ድህነት እኮ ሲያንሰን ነው???? ለራሳችን ክብር ጣውንቱ እኛው እራሳችን እኮ ነን። 
 
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር ናሬንድ ሙዲ ከአለባበሳቸው ጀምሮ #ባህላቸውን አክብረው፤ ወደው እና ፈቅደው የህንድ ትውልድ ከህይወታቸው ይማር ዘንድ ፈቅደው በየትኛውም ዓለም ዓቀፍ ጉባኤወች እራሳቸውን ሆነው፤ በተገኙበት መድረክ ሁሉ የራስን መሆን #ውስጥነት ለተተኪው ትውልድ የፊደል ገበታ የሆኑ ታላቅ ሰው ናቸው። ሁልጊዜም እመሰጥባቸዋለሁኝ። አለባበሳቸው እጅግ ይገርመኛል። ይደንቀኛልም።
 
በዚህ ምክንያት ቀደም ባለው ጊዜም ከውስጤ አክብሮት ነበረኝ፤ ዛሬ ደግሞ #ለኦርጋኒኳ ኢትዮጵያ የሰጡት ምስክርነት ኢትዮጵያ እንደ አገር #ኖቤል እንደተሸለመች እቆጥረዋለሁኝ። ጥልቅ እና ዊዝደምን ያመሳጠረን ማንነት በዚህ ልቅና ልክ ምስክርነት መስጠት የማይገኝ #በረከት ነው። ዕለቱም #ቅዱስ ነው። ቀኑን ብቻ ሳይሆን ሰዓተ ሌሊቱም ብሩክ።
 
የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስተር ናሬንድራ ሙዲ ከመፈጠሯ በፊት ፈተናን አሸንፋ ስለተፈጠረችው ኢትዮጵያ ኦርጋኒክ ተፈጥሮ ሲገልጹ ያዬሁባቸው እርግጠኝነት በራሱ ልዩ ነበር። በኢትዮጵያ ላይ ቅናት ድብን የሚያደርጋቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅቶች ማህበረ ኦነግ፤ ማህበረ ህወሃት ወዘተ፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊቃናትን ጨምሮ በኢትዮጵያዊነት ላይ ወለም ዘለም የሚሉ #ዋዘኞች፤ ሰርክ ትብትብ ፈተና እያዘጋጁ የኢትዮጵያን ሰላም የማይሹ የቅርብም የሩቅም የኢትዮጵያ ተቀናቃኞቿ ዛሬን እንዴት #ዋሉ ይሆን? ሌሊቱስ እንደምን #ይነጋላቸው ይሆን? አንጀት አርስ ብርሃን የሆነ ምስክርነት "ለአንበሳ አገር ህዝብ" እንሆ ተሸለመ። አንበሳነት ሲንኳሰስ፤ ሲጣጣል ዛሬ ግን ቀኑ ቀናለት እና ልዕለ ሆነ። ተመስገን። 
 
በውነቱ ዛሬ የኢትዮጵያ የቀደምትነት #መካሻ ቀን ነው። የፈላስፊት ኢትዮጵያ #ብቃት ልዕልና #ካሳ የተገኜበት ዕለት ነው። በሌላ አገር መሪ እንዲህ ከመሰረት እስከ ጉልላት፤ ከአነስተኛው አቅም እስከ ላዕላይ ድረስ ውስጥን በሚፈውስ፤ ውስጥን #አይዞችሁ በሚል ቃና እና ቅኔ እናት ኢትዮጵያ ዕለቷን በክብር አስተናገደች። "እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም" 
 
ኢትዮጵያዊነት ዩንቨርስቲ ገብተው ሊማሩት የሚገባ #የዕውቀት ዘርፍ ነው። ኢትዮጵያዊነት #ሳይንስ ነው። ኢትዮጵያዊነት #ፍልስፍና ነው። ኢትዮጵያዊነት #ዩንቨርስ ነው። ኢትዮጵያዊነት #ህግም ነው። ኢትዮጵያዊነት #አናባቢም ተነባቢም ነው። ኢትዮጵያ አፈጣጠሯ ኦርጋኒክ ነው። ይህን ኦርጋኒክነቷን ሊመጥን የሚችል አቅም፤ #መቅኖ አቅል፤ አደብ አጣን። ስለሆነም ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነው የምለው ለዚህ ነው። የህንድ ጠቅላይ ሚኒስተር በዚህ ልክ እኛነታችን ሲያዘክር እኛ ግን??? ስናሳዝን። 
 
እኛ የማናውቃቸውን ታሪኮች ቁጭ አድርገው መምህራችን አስተማሩን። በውነቱ #የሐዋርያነት ተግባር ፈጽመዋል። በአንድም በሌላ ኢትዮጵያ ያለባትን የውስጥ መከፋትን አጽናኝ ሆነውም አይቻቸዋለሁኝ። ከአዶሊስ እስከ ሉሲ፤ ከድሬ እስከ መቀሌ ሲነሳ በልካችሁ ላይ አይደላችሁም፤ የሚያምርባችሁ በእናታችሁ ውስጥ ስትሰክኑ ነው፥ ቅኔው ይህ ነው። ስለ እናት አገር ኢትዮጵያ ያነሱትም የእናትነትን እዮራዊ ጸጋ ከአገር ጋር? ዋው። ሚስጢር አዋቂ ናቸው።
 
ለተከበሩ ናሬንድራ ሙዲ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስተር በብልጽግና መንግሥት የተደረገላቸው አቀባበል ትልቅ ነበር። ይገባቸዋልም። ተናግረው ሲጨርሱ ቁሜ ነው ያጨበጨብኩላቸው። እናቴን ያከበረ፤ እናቴን ያወደሰ ክብሬ ነውና። እሳቸው በእንግሊዘኛ ቋንቋ እየተናገሩ በአማርኛ ቋንቋ አስተርጓሚ ሊኖር ይገባ ነበር። ህዝብ ከመንፈሳቸው ጋር መዋህድ የሚችለው፤ በስማ በለው ሳይሆን ጠረን እና ጠረን ሲዋህድ ነበር። ታቅዶም ይሁን ሳይታቀድ አላውቅም። ግድፈት ነው። አንድ አገር የራሷ ቋንቋ፤ የፊደል ገበታ እያላት ይህን መሰል ግሎባል ጉባኤ ላይ አለመጠቀም እራስን ዝቅ ያደርጋል። 
 
በመልዕክትም፥ በአንደበትም አማርኛ ቋንቋም በልኩ ተከብሯል። ሐሴት አግኝቸበታለሁም። ያው እሱም እኮ ተገፊ አይደለንም። ለባችለር፤ ለማስትሬት፤ ለዶክትሬት፤ ለፕሮፌሰርነት፤ ለሳይንቲስትነት፤ ለፈላስፋነት፤ ለዓለም ዓቀፍ ኃላፊነትም፤ ለሽልማትም አብቅቶ። ሀ ብዬ ለ ልባል ሳይባል የሚሞከር ነገር የለምና። ነፃነቱም፤ መኖሩም፤ መርሁም እሱ በእሱ ነው ዕድሜ ለአጤ አማርኛ ቋንቋ! 
 
ልጅ -- ለእናቱ? ምን ይሁንላት። ምን ያድርግላት? ለየግላችን የተሰጠ የቤት ሥራ ነው።
ከልጅ ለእናቱ? ምን ይሰጣት? ምንስ ትሸለም? በነፍስ ወከፍ የተሰጠ ፈተና ነው።
ልጆች በወልስ ምን ይጠበቅባቸዋል? ለሁላችን የተሰጠ የቤት ሥራ ነው።
በዘመናችን --- ምን አጓድለን? ምንስ ---- አሟላን?
ዕውን ኢትዮጵያ #እናታችን የማለት ድፍረቱስ አለን። እንችላለን? አቅሙ አለን? እንፈታተሽ።
በመጨረሻ የተከበሩ የህንዱ ጠቅላይ ሚር ናሬንድራ ሙዲ ለዓለም ህዝብም ስለኢትዮጵያ ታላቅ መልዕክት አስተላልፈዋል። መካች የሆነ መልዕክት ነው። ለዛውም ኦርጋኒክ የሆነ መልዕክት። እኔ ከመቀመጫየ ብድግ ብዬ ቃለ ህይወት ያሰማልኝ ብያለሁኝ። ዛሬ እምተኛው እንቅልፍ ታይቶኛል። ወህ እላለሁኝ። የቤት ሥራዬ እናት አገሬ ኢትዮጵያ ብቻ ናት። የኖርኩትም ስለእሷ ነው። ትንፋሼ ናት ትርታዬ እናት ዓለሙ ኢትዮጵያችን። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
17/12/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር @ethiopiannewsagency

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።