መዳኛችን እንዴት? መቼስ?። #ለሰውነታችን #ሰብዐዊነትን እንመግበው።
«በ60 ቀናት አሜሪካን እንዲለቅቁ የተነገራቸው ኢትዮጵያዊያን ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?»
ይህ ዘገባ የBBC ነው። ዝርዝሩ ከሥር ሙሉውን ፖስት አድርጌዋለሁኝ። መረጃው ውስጥን የሚጎዳም የሚያሳዝንም፦ የሚረብሽም ስለነበር "ለኢትዮጵውያን ይሰጥ የነበረው ከለላ መነሳቱን አንብቤ" ፈጣሪ አምላኬ #መላ እንዲያበጅለት ተማጽኜ ነበር።
የእኛ መዳኛ - ሩቅ፤ በጣም - ሩቅ መሆኑን የተገነዘብኩበት አጋጣሚ ነው። ኢትዮጵያዊ #መተዛዘን የተሰጠን ጸጋ እየሸሸን መሆኑን ተገንዝቤበታለሁኝ።
እንደምን ስደተኛ ወገናችን ተመላሽ ሲሆን ለአንድ ለራሳችን ወገን ፌስታ ሊሆን እንዳልቻለ አልገባኝም። ኢትዮጵያ እኮ ነው የምትጎዳው። ትምህርቱ ደግሞ አሜሪካ ብቻ ተንጠሌጥሎ የሚቀር እንዳይመስላችሁ። እንደ ሰደድ እሳት ሌላውም ይከተለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የኢትዮጵያ ስደተኛ በአነሰ ግምት የ5 ወገኖቻችን የጉሮሮ #ማርጠቢያ ነው። ኢትዮጵውያን አይደለም ለቤተሰብ ለጎረቤት፤ ለአብሮ አደግ፤ ለጓደኛ፤ በየዘመኑ በፖለቲካ ምክንያት #ለሚታሠሩ ወገኖች፤ እራሳቸውን ጎድተው ይረዳሉ።
ምንም የሌላቸው ግን አካፍለው ለመብላት እጀ ረጅሞች ናቸው ኢትዮጵውያን። በሌላ በኩል ለተቋማት እርዳታም ፈጣኖች ናቸው። እንደ ህዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ ሩህሩህ፤ #ቅን እና #ቀና ነው።
በተጨማሪም ደሃዋ አገራችን ኢትዮጵያ #በጦርነት፤ በተፈጥሮ አደጋ፤ በሰብአዊ መብት አያያዝ በየዘመኑ ካሉ የፖለቲካ ቀመሮች ጋር ጥግ ባላገኙ አመክንዮወች የዲታ አገሮች የኢኮኖሚ #ማዕቀብ ተጠቂ ናት።
መጠነ ሰፊም ብድርም አለባት። ይህን በተቻለ መጠን የሚያመጣጥነው ስደት ላይ ያለ ወገን ለቤተሰብ፤ ለወዳጅ፤ ለጎረቤት ሳይቀር በሚያደርገው እገዛ ኢትዮጵያ በተወሰነ ሁኔታ #የውጭ #ምንዛሬ ዕድል የማግኜት አጋጣሚ አላት።
እንዲሁም ኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ ምስቅልቅል በጦርነትም፤ በጥላቻም፤ ከተሞችን ለማሳመር በሚወሰደው የኮሪደር ልማት እርምጃም፥ አዲስ ከተማ በመመሥረት ሂደትም በአንድም በሌላም በብዙ ወገኖቻችን #ተፈናቅለዋል።
ከተመላሾቹ ውስጥ ቤተሰቦቹ የተፈናቀሉ እና መግቢያ የሌለውም ወገን ሊኖረን ይችላል። ይህ ምኑ ያስደስታል? ይሄ ምኑ ያስዳንሳል? ቢያንስ ሰው መሆን እንደምን ያቅታል? ለሰው ልጅ ታላቅ አክብሮት ያላት የሃይማኖት አገር ተፈጥረን ስለምን መጨካከንን እናባብላለን? ለምን?
ሌላ በሊስት ተዘረዘሩ ፖለቲከኞችም ወደ መገር ሊመለሱ ተብሎ ፌስታ ሆኗል። ብዙው ፖለቲከኛ እኮ ለራሱ ቁራሽ እንጀራ ሳያጣ የሚሰደድ ነው። ያው የማይደረስበት ዲሞክራሲ በሚል ሞቶ ነው መኖሩን የሚገብረው።
ህም፦ ኧረ እና ምን እማላዝንበት ጉዳይ አለ?? እስር ቤት ያሉ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ዘንድ የበኩላችን እየደከምን የተጨማሪ ፖለቲከኛ እስር፤ እንግልት፤ የቤተሰብ ሃዘን፤ ሁሉም እናት አለው እና #የእናት ሃዘን መሳቀቅ - ስጋት እና ፍራቻን መናፈቅ ከየትኛው የጭካኔ ዓይነት ይመደብ??
ጨዋቲን ጨዋታ ያነሳዋል ይላሉ ጎንደሬወች። በዛ ሰሞን ዶር ገዱ አንዳርጋቸው ሥራ ሠሩ ተብሎ እንደ ነወር ሲታይ ነበር። ለትውልዱ ታላቅ አብነት ነው እኔ ያዬሁት ነገር ዕውነት ከሆነ።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ፖለቲከኞቹ የገዘፈ የፖለቲካ #ፕሮፋይል አላቸው። ሌሎች አማራጮችም በስፋት ይኖራቸዋል። ዓለም ዓቀፍ ህግ፤ ዓለም ዓቀፍ የስደተኛ አያያዝ ድንጋጌወችም አለ።
እርግጥ ባለመታደል ሃሳባችን የተበተነ፤ መንፈሳችን የተለያዬ ስለሆነ እንጂ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ህግን የሚያስተምሩ ኢትዮጵውያን ወገኖቻችን አሉን እኮ።
የተማሩትን የማያስጠጋ፤ የተማሩትን የሚያሳድድ፤ የተማሩትን በዘመቻ የሚያዊክብ #ጋድም የሆነ የፖለቲካ ባህል ኢትዮጵያ ስላላት እንጂ ያለው አቅም #አቅም መሆን ቢችል፤ የተደራጄ ንቅናቄ በህግ አግባብ ቢያደርግ መመከት ይቻል ነበር።
በዘመነ ህወሃት ወዳጄ አቶ #ኦባንግ ሜቶ ይህንን የሚደፍን አቅም ነበረው። እሱን የበላ ጅብ አልጮህ አለ እንጂ። ኦባንግሻ "ጥቁሩ ሰው" ተቋም ነበረው "አዲሲቱ ኢትዮጵያ" የሚል። አብረውት የሚሠሩት ትህትናቸው፤ ለሴት ልጅ የነበራቸው አክብሮት በታሪኬ አይቼው እማላውቅ ልዩ፤ በጣም ልዩ ስጦታም ነበር።
የሆነ ሆኖ የወል - ሃዘን፤ የወል - መከፋት፤ የወል - ዕንባ፤ የወል - ጭንቀት፤ የወል - ስጋት፤ የወል - ችግርን #የእኛ ማለት እንደምን ያቅተን? አለመቻሊችን የሚቻል አልሆነም። በዚህም ውስጤ በእጅጉ ያዝናል።
እርግጥ ነው እንዲህ ያለ ምርር ያለ ሃሳብ ሲገባኝ አንጀቴን ያመኛል። ያመኛል። ያመኛል። ብዙ የጭካኔ ሰሞናት ሱናሜ ሲመጣ ዘወር እላለሁኝ። ምክንያቴ ይኽው ነው። ዕንባማ ነኝ። ጉዳቱ ከዓይንም አልፎ አንጀትንም ሆነ። ምንም አላድርግለት ወገኔ እንዲከፋው፣ ጥቁር እንዲለብስ፣ እንዲጨነቅ አልሻም። በፍጹም።
የእርግማን ይሁን አላውቅም። አንድን ሰው የሆነ ሰብዕና ምንም ቅጥልጥል ሳያስፈልገን፤ #ከፖለቲካ ውጭ ለማየት እንደምን አቃተን???? ሰው እኮ ከፈጣሪ በታች ለእኛ አገልግሎት ከተፈጠሩ ተቋማት ሁሉ ይበልጣል።
የእስከ ዛሬው መጨካከናችን - አላተረፈንም። መገፋፋታችን - አልጠቀመንም። መለያዬታችን - አልቀናንም። መገዳደላችን በምድር ወንጀል በሰማይ ሃጢያት ነው። ከዚህም አልታቀብንም። ፈጣሪ ይቅር ይበለን። አሜን።
ዛሬም እንደ ትናንቱ #የወደቅንበትን ጎዳና ለምን እንመርጣለን? ስደት ላይ ያሉ ብዙ ወገኖቻችን አይናገሩትም እንጂ ፈተናቸው መጠን የለውም። እንኳንስ ዘመን ሙሉ ለተወሰነ ደቂቃ #ስደት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ሲያስቡትም፤ ሲኖሩበትም #ሲቃ ነው።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
16/12/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ለሰውነታችን ሰብዐዊነትን እንመግበው።
================/////=======--=======///----=======-----
#የBBC ዘገባ ………
"በ60 ቀናት አሜሪካን እንዲለቅቁ የተነገራቸው ኢትዮጵያዊያን ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?"
"ከ 2 ሰአት በፊት የአሜሪካ መንግሥት ከሦስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያውያን በጊዜያዊ የሕግ ከለላ በአገሪቱ ውስጥ እንዲኖሩ እንዲሠሩ የፈቀደበትን አሠራር እንዲያከትም ወስኗል።"
"በትግራይ ጦርነት ምክንያት በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለኢትዮጵያውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ሲሰጥ የነበረው ጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ መነሳቱን ተከትሎ፤ ከለላው ተሰጥቷቸው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ከአሜሪካ ለመውጣት የ60 ቀናት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።"
"የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ ክሪስቲ ኖም "የአገሪቱን ሁኔታ በመመርመር እና ከሚመለከታቸው የአሜሪካ መንግሥት አካላት ጋር በመመካከር" ኢትዮጵያ ለጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን "የማታሟላ አገር ናት" የሚል ውሳኔ መተላለፉን አስታውቀዋል።"
"በ60 ቀናት አሜሪካን ለቅቀው እንዲወጡ የተነገራቸው ኢትዮጵያዊያን ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? ጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ የሚሰጥባቸው ሁኔታዎችስ የትኞቹ ናቸው? የሚለውን በተመለከተ በአሜሪካ ከአሥር ዓመት በላይ የሠሩትን የሕግ ባለሙያ ሙሉዓለም ጌታቸው አድገህ አነጋግረናል።"
"ጊዜያዊ ከለላ ምንድን ነው? በምን ዓይነት ሁኔታስ ይሰጣል?"
"የአሜሪካ መንግሥት ጊዜያዊ ጥበቃ ወይም ከለላ መስጠት የጀመረው በአውሮፓውያኑ 1991 ሲሆን፤ ይህ መብት የሚሰጠው በአገራቸው ግጭት፣ ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ ወይም ሌላ ለደኅንነታቸው አስጊ የሆነ ክስተት ለገጠማቸው ስደተኞች ነው።"
"Temporary Protected Status ወይም TPS ከተሰጣቸው አገራት መካከል ሶማሊያ እና ሶሪያ (ከጦርነት ጋር በተያያዘ) እንዲሁም ኤል ሳልቫዶር (ከርዕደ መሬት ጋር በተያያዘ) ይጠቀሳሉ።"
"ለአንዳንድ አገራት እስከ 20 ዓመት የዘለቀ ከለላ ተሰጥቷል። ለምሳሌ የሶማሊያ ጊዜያዊ ጥበቃ ከ1994 ጀምሮ እስካሁን ድረስ ቆይቷል።"
"እንደ ስሙ ጊዜያዊ ነው። ቋሚ እንዲሆን ታስቦ አይደለም የተዘጋጀው" ሲሉ የሕግ ባለሙያው ሙሉዓለም ጌታቸው ይገልጹታል።"
"የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ለስደተኞች የሚሰጠውን ጊዜያዊ ከለላ በየጊዜው ያድሳል። ጥበቃው የሚደረግላቸው ሰዎች አሜሪካ ውስጥ የመሥራት መብት አላቸው።"
"ጊዜያዊ ከለላ እንደ መኖሪያ ፈቃድ ወይም እንደ ዜግነት የሚወሰድ አይደለም። በከለላው ሥር ያሉ ሰዎች የሕጋዊ ጥበቃው ቀነ ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላ ከአሜሪካ መውጣት ወይም ለሌላ ዓይነት የስደተኞች/ጥገኝነት ጠያቂዎች ከለላ ማመልከት አለባቸው።"
"የአሜሪካ መንግሥት ይህንን ሕጋዊ ጥበቃ በመጀመሪያ ለ18 ወራት ተግባራዊ እንዲሆን ለኢትዮጵያውያን መስጠት የጀመረው ጥቅምት 11/2015 ዓ. ም. ነው።"
"በወቅቱ በዋነኛነት የትግራይ ጦርነትን ጨምሮ በአገሪቱ ውስጥ ውስጥ የነበረውን የትጥቅ ግጭት፣ የተለየ እና ጊዜያዊ ሁኔታን ከግምት በማስገባት በአሜሪካ ውስጥ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ጊዜያዊ ሕጋዊ ከለላ እንዲያገኙ ተፈቅዶ ላለፉት ሦስት ዓመታት ተግባራዊ ሲሆን ቆይቷል።"
"እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ጊዜያዊ ከለላ ሥር ከተካተቱት መካከል አገራት ሄይቲ፣ ቬንዙዌላ፣ አፍጋኒስታን፣ ካሜሩን፣ ሱዳን፣ ዩክሬን፣ ኤል ሳልቫዶር፣ ሆንዱራስ፣ ኒካራጉዋ ይገኙበታል። ከዚህ ቀደም ላይቤሪያ፣ ቦስኒያ-ኸርሴጎቪና እና ኩዌት ጥበቃ ተሰጥቷቸው ነበር።"
"ለኢትዮጵያውያን ተሰጥቶ የነበረው ጊዜያዊ ሕጋዊ ከለላ የሕግ ባለሙያው ሙሉዓለም እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ የተካተተችው በታኅሣሥ 12/2022 ሲሆን ከለላው ተሰጥቶ የነበረው ከአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2022 በፊት ወደ አሜሪካ ለገቡ ሰዎች ነው።"
"ይህንን ፈቃድ የቀድሞው የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለ18 ወራት አራዝሞት የነበረ ሲሆን፤ የከለላው ቀነ ገደብ የተጠናቀቀው ታኅሣሥ 12/2025 ነው።"
"ይህ ማለት ከታኅሣሥ 12 ጀምሮ ያልቃል ማለት አይደለም። የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እንደገለጸው የሚያበቃው የካቲት 12/2026 ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።"
በዚህም መሠረት በጊዜያዊ ጥበቃ ሥር ያሉ በቀጣይ 60 ቀናት ውስጥ ከአሜሪካ እንዲወጡ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል። ከዚያ በኋላ የሚቆዩ ሰዎች "ከከለላ ውጭ" እንደሚሆኑም የሕግ ባለሙያው ይናገራሉ።
"አምስት ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን እና ከኢትዮጵያ የሄዱ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰዎች በዚህ ከለላ ሥር እንደነበሩ ተገልጿል።"
"በጥበቃው ሥር ተካትተው የነበሩት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ መዳረሻቸው ኢትዮጵያ የሆነ (ኢትዮጵያ ቆይተው አሜሪካ የገቡ) የተለያየ አገር ዜጎችም ጭምር ናቸው።"
"ፓስፖርታቸው የኢትዮጵያ ባይሆንም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ለአደጋ እንዳይጋለጡ ከለላ ይሰጣቸዋል" ይላሉ ባለሙያው።
"ጊዜያዊ መቆያው የሥራ ፈቃድን ስለሚያካትት ለስድስት ወይም ለ18 ወራት አልያም ደግሞ ለሁለት ዓመት መሥራት ይችላሉ።"
"የሕግ ባለሙያ ሙሉዓለም እንደሚሉት በቀጥታ በጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ ሥር ብቻ የነበሩ እና በሌላ የስደተኞች/ጥገኝነት ጠያቂዎች ከለላ ሥር ያልተካተቱ ኢትዮጵያውያን "በግምት 1000" ቢሆኑ ነው።"
"አምስት ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በዚህ ከለላ ሥር እንዳሉ ቢነገርም አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ከጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ በተጨማሪ ሌሎችም የከለላ አሠራሮች ሥር የተካተቱ ናቸው።"
"በጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ ሥር ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር "ብዙ የሚባል አይደለም" ሲሉም ያስረዳሉ።"
"ለማነጻጸሪያነት፤ ከሶማሊያ ከለላው የተሰጣቸው ሰዎች እስከ 700 ሺህ፣ ከቬንዙዌላ እስከ 600 ሺህ እና ከሄይቲ እስከ 500 ሺህ ይደርሳሉ።"
'በጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ ሥር ሆነው የተማሪዎች ቪዛ (ኤፍ1) ወይም ሌላ ከለላ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ የሚጠቅሱት ባለሙያው "ቲፒኤስን የሚፈልጉት ጊዜያቸው ሲያልቅ [ወደ አገር ቤት] ላለመመለስ እና ለሥራ ፈቃድ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።"
"በጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ ሥር በአንድ ወር ውስጥ አመልክቶ የሥራ ፈቃድ ማግኘት ይቻላል። ከሌሎች ከለላዎች በተሻለ ፈጣን የሥራ ፈቃድ ማግኛ መንገድ ሲሆን፣ ገደብ የሌለው የሥራ ፈቃድ በመሆኑም በማንኛውም የሥራ ዘርፍ መሰማራት ይቻላል።"
"ይህ ጊዜያዊ ሕጋዊ ጥበቃ ለኢትዮጵያውያን በተፈቀደበት ጊዜ ወደ 27 ሺህ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቅ እንደነበር በወቅቱ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ገልጾ ነበር።"
"የዚህ ጥበቃ ተጠቃሚ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ውሳኔው ይፋ ከመሆኑ በፊት በአሜሪካ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ የቆዩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸው የነበረ ሲሆን፣ ከተጠቀሰው ጊዜ በኋላ ወደ አሜሪካ መግባት ለዕድሉ ተጠቃሚ እንደማያደርግ ተግልጾ ነበር።"
"ከሌሎች የስደተኞች ጥበቃዎች በምን ይለያል?"
"ኢትዮጵያውያን ከለላውን ለማግኘት ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ መሄዳቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር።"
"ከጥቅምት 2022 በፊት ወደ አሜሪካ ለገቡ ሰዎች ከለላው ይሰጥ የነበረ ሲሆን፤ ሕጋዊ ጥበቃው ባለበት እንዲጸና በዚህ ወቅት ወደ አሜሪካ ከገቡ በኋላ በተከታታይ አሜሪካ ውስጥ መኖር ግዴታቸው ነው።"
"ለምሳሌ ወደ ኢትዮጵያ ወይም ወደ ሌላ አገር ከተጓዙ ከለላው እንደሚቋረጥ የሕግ ባለሙያው ያብራራሉ።!
"ከጥቅምት 2022 በፊት አሜሪካ ከገቡ ሰዎች በተጨማሪ ከሚያዝያ 11/2024 በፊት አሜሪካ ለገቡ የተሰጠ ከለላ እንዳለ የጠቀሱት ባለሙያው፤ እነዚህ ሰዎችም ከአሜሪካ ሳይወጡ መኖር እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።"
"ከለላው ኢትዮጵያ፤ ከኢትዮጵያ ለሚመጡ ሰዎች አደገኛ ናት ብሎ መንግሥት የሚሰጠው ነው። legal notice [ሕጋዊ ማሳሰቢያ] ነው" ይላሉ።"
"ይህ ማለት ደግሞ ከለላው የተሰጣቸው ሰዎች እንደ ሌሎች ጥገኝነት ጠያቂዎች 'ኢትዮጵያ ብመለስ አደጋ ይደርስብኛል' የሚለውን ማስረጃ ማቅረብ አይጠበቅባቸውም።"
"መንግሥት አደገኛ ነው የሚለውን ተረድቶ የሰጠው ከለላ በመሆኑ #ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ አገራቸው መመለስ ለአደጋ እንደሚያጋልጣቸው የማሳመን ሕጋዊ ግዴታ (legal burden) የለባቸውም።"
"የኢትዮጵያዊያን ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?"
"የሕግ ባለሙያው ሙሉዓለም እንደሚሉት፤ በ60 ቀናት አሜሪካን እንዲለቅቁ የተነገራቸው ኢትዮጵያዊያን ከጊዜያዊ ሕጋዊ ከለላ ውጭ ወደሆኑ የጥገኝነት መጠየቂያ አሠራሮች መዞር ይችላሉ።"
"በዚህ 60 ቀን ውስጥ ወደ ጥገኝነት ወይም ወደ ሌላ 'ስታተስ' ጥያቄ መለወጥ ይቻላል። ነገር ግን ከለላ እንደሚያስፈልጋቸው ለማሳየት ማስረጃ ማቅረብ ግዴታቸው ነው።"
"የሚያቀርቡት ማስረጃ ሐሰተኛ ከሆነ የአሜሪካን መንግሥት ማታለል ወንጀል በመሆኑ ለወደፊት ሊገኝ የሚችል የስደተኞች ከለላን እንደሚያሳጣቸው ያሰምሩበታል።"
"ጥገኝነት መጠየቅ ያልፈለጉ ሰዎች ከየካቲት 12/2026 በፊት ከአሜሪካ መውጣት አለባቸው።
በገዛ ፈቃዳቸው አሜሪካ ለቅቀው የሚወጡ ሰዎች አንድ ሺህ ዶላር እንደሚሰጣቸው በአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት መገለጹን በተመለከተ የሕግ ባለሙያውን ጠይቀን ይህ አሠራር ለኢትዮጵያውያን የሚተገበር አለመሆኑን አስረድተዋል።"
"በበጎ ፈቃዳቸው ከአሜሪካ ለመውጣት (voluntary departure) የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ደንበኞቻቸውን በተመለከተ ለአሜሪካ መንግሥት መረጃ ቢሰጡም፤ "ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በፈቃደኛነት የመውጣት ስምምነት ስለሌለ ራሳቸው ትኬት ቆርጠው መሄድ አለባቸው" የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።"
"አንድ ሺህ ዶላር ይሰጣል የሚለው አካሄድ "ለኢትዮጵያውያን የሚሠራ አልመሰለኝም" ሲሉም አክለዋል።"
"ለኢትዮጵያውያን ተሰጥቶ የነበረው ጊዜያዊ ሕጋዊ ከለላ መነሳቱን በተመለከ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በድረ ገጹ የሰጠው ማብራሪያ ከሌሎች ጥበቃው ከተነሳባቸው አገራት የተለየ ይዘት የለውም።"
"ለሁሉም አገራት የተሰጠው ከለላ መነሳቱን በተመሳሳይ መንገድ ነው የገለጹት" ሲሉ የሕግ ባለሙያው ይናገራሉ።"
"ለኢትዮጵያውያን ሕጋዊ ከለላው የተሰጠው በትግራይ ጦርነት ወቅት እንደሆነ ጠቅሰው "አሁንም በሌሎች ቦታዎች ጦርነቶች አሉ" በማለት የተጋረጠውን አደጋ ይገልጻሉ።"
"ኢትዮጵያውያን ሊኖራቸውን የሚችለው አንደኛው የሕግ አማራጭ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ የከፋ ሆኗል፤ በ60 ቀናት ውጡ መባሉ ትክክል አይደለም ብለው በፍርድ ቤት መክሰስ ነው።"
"ወደ ክስ ቢሄዱ [ከአሜሪካ መውጣቱን] ለጥቂት ወራት ሊያራዝመው ይችላል" ይላሉ የሕግ ባለሙያው።
"ሌላኛው አማራጭ መንግሥት አንድ ሺህ ዶላር እንደሚሰጥ ቢያስታውቅም ተግባራዊ አልሆነም በሚለው መክሰስ መሆኑን ይጠቅሳሉ።"
"መንግሥት አታሎናል፤ አንድ ሺ ዶላር አልሰጠንም ብለው ፍርድ ቤት ሊወስዱት ይችላሉ።"
ጊዜያዊ ሕጋዊ ከለላቸው በመነሳቱ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ከወሰዱ አገራት መካከል ሶሪያ እና ቬንዙዌላ ይጠቀሳሉ።"
"የቬንዙዌላ ከለላ መነሳቱ ትክክል አይደለም በሚል በታች ፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተመልክቶት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ውሳኔውን የማስተላለፍ ሥልጣን አለው ሲል በይኗል። በሌላ በኩል ደግሞ ለሶሪያ የተሰጠው ከለላ ለተጨማሪ ቀናት/ወራት እንዲራዘም ተወስ"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ