#አትሞክረው። የፖለቲካ ድርጅት #ኮንፓሳችን #መመሥረትም #መምራትም #የጫጉላ #ሽርሽር ስላልሆነ።

 

«አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።» አሜን።

 
 
እንዴት ሰነበት ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ። እንኳን በህይወት ኑረህ ለመተያዬት አበቃን። ተመስገን። ስክነትህን እማከብረው ቁምነገር ነበር።
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች አቶ እስክንድር ነጋ ገና ከእስር ቤት እንደወጣ ጉዞውን ሳይጀምር ነበር #ፋኖን እመራለሁ እንዳትል ብዬ የፃፍኩት። ለምን? የፓርቲ አደረጃጀት መርህ ስለማይፈቅድለት። 
 
ከዚህ በላይ መሄድን አልፈቅደውም። ሰሚ ጠፋ እና የሆነው ሆነ። ለአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ሌላ ዕዳ እንደሚገጥመው በትክክል አውቀው ነበር። በሆነ ነገር ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ይቻላል በአቦ ሰጥም ሊገኝ ይችላል። 
 
መሪነት ግን #አቦሰጥ አይደለም። የበዛ አደብ። የበዛ አቅል። የበዛ ተመክሮ። የበዛ ክህሎት ብዙ በጣም ብዙ ርቁቅ አመክንዮ ይጠይቃል። ቅደም ተከተሉ በተበተበ ገጠመኝ ህዝብን ለማገዶነት ማጨት የላይኛው ይመዝነው። 
 
ስንት ትጉኃን ሰብሰብ ብለው የተቀመጡትም ከውጥኑ ለክተውት ነው። ይህም ሆኖ ብዙ አመክኒያዊ ጭብጦችን አቅርቤ መሞገት ስችል በጣም የበዛ ዝምታን መረጥኩኝ። 
 
በዚህ ጉዳይ ቅንጣት ብየ አላውቅም። በየጊዜው እንደ ጉልት ገብያ ድርጅት ተመሰረተ፣ ፈረሰን እሰማለሁኝ። ፔጄን በዚህ ዙሪያ አላስጨነቅኩትም። 
 
ዝም ብየ ነበር የወገኖቼን #ጉዳት ከአለም ዓቀፍ ሚዲያ ሳገኝ ብቻ ስዘግብ ነበር። ሙግቱን ብጀምረው ብዙ በጣም ብዙ ነገሮች ሊሰባበሩ ስለሚችሉ በዝምታ ተባጄ።
 
#የሆነ ሆኖ ……
 
ካፒቴን ፻አለቃ ማስረሻ ሰጤ የረጋ ሰብዕና አይበታለሁ። በዘመነ ህወሃት ዋጋ ከከፈሉት ውስጥ አንዱም ነው። ብዙ መከራ አሳልፏል።
ከእስር ከተፈታ በኋላም ጊዜ ሳያጠፋ በተፈቀደለት ክልል እየተዘዋወረ የአማራ ወጣቶችን አደራጅቷል። ሌሎች ይህን ዘርፍ ሳያስታውሱት ከአማራ ክልል ውጪ ለሆኑ አማራወች ተስፋ የመሆን ዝንባሌ ነበረው። ብቸኛም ነበር። ጠንክሮ በቃለ ምልልሱ ስላልተነሳ ነው ማጠናከሪያ መስጠት የፈለግሁት። ከውስጤ ነው ሁሉንም ነገር የምከታተለው።
 
ካፒቴን ፻ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ሰላማዊ ኑሮን መምረጡ መብቱ ነው። የተገባም ነው። አቅም ለክቶ መወሰን ብልህነት ነው። መቅደምም ነው። ቃለ - ምልልሱን አየር ላይ ነበር የተከታተልኩት።
 
ይጸጸታል ቁሞም ተንበርክኮም ለጠፋው ሁሉ ይቅርታ ይጠይቃል ብዬ አስቤም ነበር። ጸጸት የለበትም። ለዛ ሁሉ ድቀት፣ መከራ፣ የመኖር የገዘፈ መስተጓጎል፣ የታዳጊ ወጣቶች የእውቀት ተስፋ ወደ ማህይምነት መመለስ፣ የጠፋው ነፍስ፣ የንጹሁ ገበሬ ስቃይ እና ፈተና፣ የአገልግሎት ተቋማት የገጠማቸው ችግር፣ የገዳማት ያ ሁሉ ፈተና፣ ተዘርዝሮ የማያልቅ ወዘተረፈ ፈተና የአማራ ህዝብ አስተናግዷል። ክብሩም አብሮ ተማግዷል። ተስፋው ተጎሳቁሏል። 
 
ለዚህ ሁሉ መከራ የመፍትሄ መንገዱ ይህ ነው ብሎ የመከረ፣ የወሰነ፣ የወጠነ #መሪ የ፻ አለቃ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ አሻግሮ ሰላማዊ ተቃውሞ ሳለ ተነጋግረን ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ጥፋት አይደርስም፣ ከማለት እንዲህ እሱ ሰላሙን ሊመርጥ ለዛ ሁሉ ቅን ማገዶ የራሱን ድርሻ ወስዶ እራሱን ሊወቅስ፣ ምህረት ቅኑን የአማራ ህዝብ ሊጠይቅ ሲገባ በዝምታ አልፎታል። ውስጤም አዝኗል። 
 
ሌላው የአህጉሩን ችግር በአህጉሩ ስለመፍታት ቲወሪው ጥሩ ነው። ግን የመልሶ የማቋቋም ድጋፍ አፍሪካ ህብረት ይችላልን? ደረጃውስ? ዓለም ዓቀፋ ወይንስ አህጉር አቀፋ የትኛው ነው ታላቁ የመደራደር ዕውቅና።
 
ይህን እንደ አልባሌ ነበር ያለፈው። ጠፍቶት አይደለም። ስላልቻለ ብቻ እንጂ መሻቱ ደረጃው ከፍ ቢል ማን ይጠላል? ለገዘፈ መስዋዕትነት የተገባ፣ ደረጃውን የጠበቀ ዕውቅና መጠበቅ ይገባል። ግን ለመደራደር አቅም ይጠይቃል። 
 
ሌላው የብልጽግና መንግሥት #አላተረፈም ሲባል ሰምቻለሁኝ። ከዚህ በላይ ትርፍ ምን ያግኝ? አስኳሉ ላይ ነው ያለው አመክንዮው። ቀሪው ግንጥል የድርጅቱ አካል ህልውና በቀጣይ ምን እና ምን ሊሆን ይችላል? በቀጣይ የመደራደር አቅሙስ? ይህ ብቻ አይደለም።
የነበረበትን ድርጅት እኮ ልጥ ወይንም ሲደርቅ ቅርፊት ነው ያደረገው። ድርጅታቸው አለም፣ የለም ለማለት ቃላት የለውም። 
 
በሌላ በኩል ካፒቴን ማስረሻ ብዙ ምስቅልቅሎች መፈጠሩን በኩራት ሲገልጽ ሰምቻለሁ። በቀደመ ቃለ ምልልሱ ሳውቀው ሙሉ ኮንፊደንስ አይቼበት ነበር። በትናንት ቃለ ምልልሱ በቀደመው ልክ ኮንፊደንሱን አላየሁም። 
 
#ትልቁ በኽረ ጉዳዬ።
 
ዋናው ጉዳዬ ካፒቴን ፻ አለቃ ሰጤ ድርጅቱን በምርጫ ቦርድ አስመዝግቦ ለዚህ ዓመት ባይቻል ለሚመጣው ምርጫ ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ገልፆል።
 
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች "ላም እረኛ ምን አለ?" የሚለውን አያዳምጡም እንጂ #አይሞክረው ባይ ነኝ። በፍጹም ሁኔታ የአንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪ የመሆን ምንም አቅም እንደሌለው ነው እኔ ያዬሁት።
 
አቅም ቢኖር ስንት ጊዜ ድርጅታቸው #ፈረሰ ተሰራ??? ምንስ አሳኩ? #ከመርዶ በስተቀር። 
 
እራሱ አሁን ከብልጽግና መንግሥት ጋር በምን ተደራደሩ? ምን አተረፋ? ምን አገኙ? በአማራ ጉዳይ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች ተፈቱን? የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ የራያ ጉዳይ የመጨረሻ #ውሳኔ አገኜን????
 
ለመሆኑ በድርድሩ የአፈፃጸም ሂደት ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም ብልጽግና ወይንስ ቲም ካፒቴን? የትኛው ነበረ ከላይ? ድርድርን ለስኬት የሚያበቃው አቅም ስለሆነ?
 
ይህን ያዬ የአማራ ልጅ ምን አተርፋለሁ ብሎ የዕድሜ ብክነት ይፈቅድ ይሆን? ምን ሊያስገኝ በአዲሱ የቲም ማስሬ የፖለቲካ ድርጅት?
ካፒቴኑ እንደ እኔ እንደ ሥርጉትሻ ዕይታ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት አቅም አላየሁም። መሪነት ኦራተርነትም ይጠይቃል። ይህንንም በቃለ ምልልሱ ፈለግሁ አላገኜሁም። ቅብዓ ይኖርም ይሆን ብዬ ደግሜ ከውስጤ እያዬሁ አዳመጥኩት። አላየሁም።
 
ድርጅቱን በሰላማዊ ታጋይነት ቢመዘገብለት የምርጫ ቦርድ በጀት፣ የሚዲያ ሽፋን፣ ሊገኝ ይችላል።
 
ሌላውካፒቴን ማስረሻ ምርጫው ማን #ፈርስት እንደሆን አላውቅም። በመረጠው ጎዳና ይምጣ ወይንም ይወስን ለኢትዮጵያዊነት፣ ወይንም ለአማራው ውስብስብ የፖለቲካ ሁነትም የሚሆን አይደለም።
 
ተጨማሪ የአማራ ወጣትን #ለማገዶነት ለማቅረብ ካልሆነ በስተቀር ለፖለቲካ ድርጅት አደረጃጀት እና አመራ እንዲህ እና እንዲያ የሚሆን አይሆንም። የፖለቲካ ድርጅት ሞባይል መኪና ወይንም ኪወስክ አይደለምና።
 
#ለምን አይችልም አልኩ? 
 
የመሪነት አቅም አላየሁምና። ደግሞ የአማራ ትውልድ በቃው ተማገደ በየዘመኑ። ያለው ይበቃል። በአዲስ ሥም፣ በአዲስ ዝና መቀቀል በቃ! ባይ ነኝ። 
 
ለዚህም ነው አዲስ ተደራጄ፣ ተዋህደ፣ ተቀላቀለ ሲባል ፔጄ በፍጹም ሁኔታ የማያስተናግደው። ዓርማው እራሱ ስልችት ብሎኛል። የሚገርመው የማያነቡት ማኒፌስቶ ተዘጋጄ ተብሎ ሽብሸባውን ሳይ እስቃለሁኝ። መቼ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ማኒፌስቶ ገዝቷቸው ያውቅና? 
 
የሆነ ሆኖ መሪነትን መመኜት ለሳምሶናይት ማራኪ ነው። የመሪነት ሁነቱን ሳይ ግን እንደ #ልዝ እንጨት ሆኖ ነው እማየው። ፍዝነትም አለ ሲናገሩ እንቅልፍ እንቅልፍ ያሰኛችኋል። 
 
ልዝ እንጨት ወይ አይነድ፣ ወይ አያነድ ነው። ፍዝም ድንዝዝ ነው። በዚህ ሂደት የክትክታ፣ የወይራ እንጨት አይደለም የሚማገደው #ትውልድ ነው። የሚንቀለቀለው ተስፋ ነው። የሚጨማተረው ታሪክ ነው።
 
የአማራ ህዝብ ታሪክ ዛሬ ምን እና ምን እየሆነ እንደሆን እያዳመጥን ነው። በተለይ ርህራሄው፣ በህግ አምላክነቱ፣ ተፈጥሮ ወዳጅነቱ፣ ያን የከበረ፣ የተደላደለ ብቃት፣ ልቅና ጨዋነት ሃይማኖታዊነት፣ ሰብአዊነት፣ ተፈጥሯዊነት እየተንገላታ ነው። ትርፍና ኪሳራ በመንፈሳዊ አቅም መለካት ስለማይቻል #ዝም ይሻላል። 
 
የካፒቴን ፻ አለቃ ማስረሻ አራስ እህቱ ምን ያህል እንደተሰቃዬች አይቼ ስሞግት ነበር። የወላጆቹም ኑሮም አይቻለሁ። የረባ ቤት እንኳን የላቸውም። አስተምረው ምን አገኙ? 
 
እኔ ምርጫዬ አለልኩ በተሰፋ ገበርዲን ከሚጨናነቅ ማህበረ ብልጽግና ካመኑት ወደ ሙያው፣ ካላመኑት ሠራዊቱን መልሶ ካደራጄ፣ መኖራቸውን መልክ ካስያዘ በኋላ መኖርን በአዲስ ሰብዕና ቢጀምረው ምርጫዬ ነው። ለፖለቲካ ድርጅት መሪነት ግን እእ። 
 
እንዲያውም አሁን ሚዲያ ላይ መውጣት አልነበረበትም። ቢያንስ ሁለት ፯ #ጥሞና ማድረግ ይገባው ነበር።
 
በዚህ አጋጣሚ አቶ አንዷለም አራጌን ከልብ አመሰግናለሁ። ነፍሳችን አሳርፏታል። ሰብሰብ ብሎ ተቀመጠ። በእሱ ምክንያት #የጠፋ ነፍስ የለም። የተስተጓጎለ የትውልድ #ዕድሜ የለም።
 
ጎንደሮች ባለ ቅኔ ናቸው "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል።" ይላሉ። ልኩን አውቆ ቤተሰብን፣ ህዝብን ሳያስጨንቁ በአርምሞ መቀመጥን መፍቀድ ታላቅነት ነው።
 
#ታናሼ ሆይ!
 
ለአንተ ሰብዕና የፖለቲካ ድርጅት መሪነት ልኩ አይደለም። ወይ ጥብቆ ወይንም ልቅ ነው። በዘመነ ህወሃት አንተ እና ቤተሰብህ ብቻ ተማገዳችሁ።
 
1) ላልቀጠለ ድርጅትህ ምን ያህል ነፍስ ዋጋ ከፈለ?
2) ምን ያህል ጎጆ ፈረሰ? ምን ያህል ባድማ ወና ሆነ? ምን ያህሉ ምድር ውስጥ አረጁ?
3) ምን ያህሉስ አካላቸው ጎደለ?
4) ምን ያህል ሥልጣኔ ዳጥ ሆነ? ቁጭ ብለህ እሰበው። የሰው ልጅ #ዳንቴል አይደለም። ወይንም የሰው ልጅ #በፋፍሪካ አይመረትም።
እንደ ገና በሌለ አቅምህ ለምትወጥነው የፖለቲካ ድርጅት መዋለ መንፈስ፣ መዋለ ንዋይ፣ መዋለዕድሜ ይፍሰስልህ ወይንስ ይደፋልህ?????? ደግመህ ደጋግመህ እባክህ እሰበው። 
 
#ሌላ ስለሚዲያ ያነሳኽው ነው። 
 
አደባባይን ከፈቀድክ አይቀሬ ነው ሁሉም ነገር። ትችቱም - ውዳሴውም። የምትታገለው ለሃሳብ ነፃነት ከሆነ ጉሮሮው ይዘጋ አስተያዬትህን አልወደድኩትም። ሥልጣኔን ማሰርም አይቻልም። ምድር አፍ ያለው መቃብር ትሁን ማለት ፍትኃዊ አይደለም።
በተረፈ ጥንቃቄ ብታደርግ ጥሩ ነው። መኖር ስላለብህ። ለሚዲያ የሚሆኑ እና የማይሆኑትንም በጭምትነት ብትመረምራቸው ጥሩ ነው ከመናገርህ አስቀድመህ። ሰው ማትረፍ እባካችሁ ልመዱ።
 
ከሁሉ ለእነዛ አኗኗራቸው በፈተና አጥር መጠራቅቅ ውስጥ ለዶልካቸው ወላጆችህ እሰብላቸው። ሌላ መከራ፣ ሌላ መንገላታት በአንተ ምክንያት ሊዩ አይገባምና። አሳርፋቸው። ወህ ይበሉ።
 
የአማራ ወጣቶች ሁሉንም በጥሞና ተከታተሉ። መኖርን ለማኖር ግድፈትን መርምራችሁ ለመዳን ወስኑ። መኖር ካንፓስም ኮንፓስም ነውና። 
 
ይህ ቃለ ምልልስ በህይወታችሁ ውስጥ ያለውን የመወሰን አቅም ደግማችሁ ሪባይዝ እንድታደርጉት ይጠቅማችኋል። መኖርን ጀምሩ። ተማሩ። አግቡ ውለዱ። የሚከብዱ ነገሮች አሉ። የሚሻለውን ከባድ ነገር ምረጡ። በተለይ ለወላጆቻችሁ እሰቡ። እዘኑላቸውም።
ዶንኪ ቲዩብ ላይ የ፭ ዓመት ህፃን የተኩሱን ድምጽ ለይታ ጢው ጢው ድው ድው ለይታ ነገረችን። ነብይ ናት። ፃድቅ ናት። መልዕክተኛም ናት። እናቷ በድንጋጤ ወቅት ደመነፍስ እንደሚሆኑም ነገረችን። ምስባእክ ነው ለእኔ። ምን ይሁን ተብላ ስትጠየቅ #ማቆም አለች። ጦርነቱን ነው። 
 
ቸር አስበን፣ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፣ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ አሜን። 
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
20/12/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
 
ሊንኩ እንሆ ………
«በዚህ ስምምነት የገንጣይ አስገንጣይ እና፤ በገንዘብ እና ጥቅማ ጥቅም የተደራጀውን ቡድን እጅ ነው የቆረጥነው_Gize Gis @NBCETHIOPIA «

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።