ልጆች እናት አለኝ፤ አባትም አለኝ ሲሉ #ፋንታዚ አይምሰላችሁ።
#ምዕራፍ ፲፮
ልጆች እናት አለኝ፤ አባት አለኝ ሲሉ ፋንታዚ አይምሰላችሁ። መኖራቸው ውስጥ እንዳሉ ቅዱስ መልዕክት ነው። ወላጆች አትባክኑ። እርፍ በሉ። እርፍ የማያደርግ ነገር ሚሊዮን የመኖር ሸክም እንደአለ አውቃለሁኝ። እኔ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ከህዝብ ጋር ነው የኖርኩት። ህዝብ ስል በስደትም ካለሁበት ስኩን የሲዊዝ ነዋሪም ጋር፤ በአንድም በሌላም በግሎባሉ መስተጋብርም ውስጥ እማገኛቸው ከሲዊዝ ውጪ የሆኑ ወገኖቼ አሉና።
የእኛ እንደሚለይ አውቃለሁኝ ፈተናውም፤ አሳሩም ሆነ እንቅፋቱ ይበረክታል። ይህም ሆኖ ግን ነገን የሚያስቡ ወላጆች፤ ስለ ነገ ግድ የሚላቸው ወላጆች ከራሳቸው በላይ ለልጆቻቸው እንደሚያስቡ፤ እንደሚጨነቁ አውቃለሁኝ። ወላጅ ስል የወለዱትን ብቻ አይደለም። ሳይወልዱ እናት፤ አባት መሆን የቻሉ።
ኃላፊነትን የመወጣት ብቃት ያላቸው ታላቅ እህት እና ወንድም፤ አክስት እና አጎት፤ በማር ልጅ ወላጅነትን የፈቀዱ፤ አደራ የተረከቡ ጎረቤቶች፤ ልጆችን ለማሳደግ የበጎ አድራጎት ተቋም የፈጠሩ ደጋጎች ሁሉ ወላጅ ናቸው።
... እና እነኝህ ቅን ወገኖች ለልጆቻቸው ከሚጨነቁት፤ ከሚጠበቡት በላይ ለራሳቸው ህይወት ሊያስቡለት ይገባል ብዬ አምናለሁኝ። ዕምነቴ ከዕውነቴ የመነጨ ነው። የአገሬን የገጠሩንም የከተማውንም ኑሮ በተወሰነ ደረጃ አይቸዋለሁኝ። ስደቱንም እንዲሁ። ወላጆች፤ የልጆችን ኃላፊነት የተረከቡ ደጋጎች ሁልጊዜ ይባክናሉ። ብክነቱ ለልጆች ነው።
ግን ይህ ዕሳቤ ይቋረጣል። አንድ ቀን። ካለ ቀኑ፤ ካለጊዜው ይቆረጣል። ውጥኑ ሳይቋጭ ሊሆን ይችላል። ኢብን ውጡኑ ቢቋጭ እንኳን እናት የለኝም፤ አባት የለኝም ማለት መኖር የለኝም ማለት ነው። እና ዘራችሁ ዘለግ ያለ ተስፋ እንዲኖረው የራስ ጥበቃ በእጅጉ ያስፈልጋል። እናታቸውን ወይንም አባታቸውን ወይንም አሳዳጊወቻቸውን ጊዜ ሰጥተው ትኩረት ያልሰጡ፤ እያሉ ዋጋው የቀነሰ የወላጅ መኖር ቅዱስ መንፈስ ሲታጣ ቀፎ ይሆናል መኖር።
ለልጆች የሚጠቅመው ወላጆች እራሳቸውን ጠብቀው ቢኖሩላቸው ነው። ለወላጆችም የሚጠቅመው ልጆች ጊዜውን ተሻምተው ለወላጆቻቸው ሊያደርጉት የሚገባውን ሁሉን ነገር ማድረግ ሲችሉ ነው። ይህን መስተጋብር በቅጡ #ማኔጅ ማድረግ ከተቻለ መኖር ሳይጎድልበት ከፈጣሪ በታች ባሉ፤ ፈጣሪ በሰጠን የመኖር ጸጋ ልክ መኖርን ማኖር ይቻላል። ልጆች የወላጆቻቸው ወይንም የአሳዳጊወቻቸው አንባሳደር ናቸው በተፈጥሯቸው።
ወላጆችም ይሁኑ የልጆች አሳዳጊ ሰብዕናወች ወይንም ተቋማት የልጆቻቸው አንባሳደሮች ናቸው። በወላጆች እና በልጆች መካከል ውህድ የአገርነት ባህሬ ተመስጥሮ አለ። ይህን ቅኔ መፍታት የሚችሉ የተሰጣቸው በህይወታቸው ከጸጸት ሊድኑ ይችላሉ። በ፭ ዓመት እየቻለ፤ እየቻለች ወላጃቸውን በአካል ማየት ያልፈቀዱ፤ በስልክ ለማግኜት ሳንቲም ሲቆናቆኑ የኖሩ ያ ተናፋቂ ድምጽ በጥሪው በሥጋ ሲለይ ባዶነት ይሰፍናል።
ያን ወናነት የሚፈውስ አንዳችም ክስተት አይኖርም። ስብራቱን መጠገን አይቻልም። በተለይ ስደት ላይ ያሉ ልጆች ዘመን በሰጣቸው ዕድል የወላጆቻቸውን ትንፋሽ ዕለት ተለት ሊሰሙ ይገባል። መኖራቸው መልዕክተኝነቱን የሚያረጋግጠው በዚህ ዕድል ብቻ ነው። ልጆች እናት አለኝ፤ አባት አለኝ ሲሉ የመኖራቸው መልዕክት መዳፍ ላይ ይሆናል። ይህ እንዲሆን ግን ወላጅን ማኖር የሚቻልባቸው ሁሉም ነገር ሊሰጠው ይገባል።
ይገርመኛል በወላጆቻቸው ጉዳይ ስልቹወች እና ኃላፊነትን የሚሸሹ ፍጥረቶች። ይደንቁኛል ብክን ብለው ያሳደጓቸው እህት እና ወንድሞቻቸውን እየቻሉ በራስ ወዳድነት ጉዳይ ሳይሏቸው ጊዜ የሚያባክኑ። መኖራቸው መሠረቱም ታህታዩ ይሁን ላዕላዩ ወላልቆ ግን ኖርክ ሊሉ ይችሉ ይሆናል። ነዳላ መኖር እለዋለሁ ይህን።
አንድ ጊዜ ዕድል ቀንቶ ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል፤ ያን እንደ ታቦት እየተሳለሙ ኖርን ሲሉ ትነት መሆኑን ልነግራቸው እወዳለሁኝ። ለምን መኖር ሁልጊዜ አዲስ ነው። የለት ተለት ትጋት ይጠይቃል። ትናት በልተን አድረን በጥዋቱ ቁርስ ይጠይቃል አቶ መኖር። ቁርስ ተበልቶ ምሳን ይጠብቃል። መኖር ለመኖር ያልተቋረጠ ክትትል ይጠይቃል።
በስተቀር መኖር ሞናትነስ ይሆናል። ይህን የፈቀዱ ሰብዕናወች መኖራቸው ተሰቅዞ እያሰቃዩት ስለመሆኑ ልገልጽላቸው እፈልጋለሁኝ። ልጅ ልጄ ብሎ የሚያሳድግ ታላቅ እህት እና ታላቅ ወንድም፤ የወላጅ ወላጆች በጎንደርኛ እሚታ፤ አክስት አጎትም ቢሆን በአለ ጊዜ፤ በህይወት ዘመኑ ውስጥን ሰጥቶ መመረቅ መታደል ነው።
ሳይደረስላቸው ያመለጡ ወላጆች እናትም ይሁን አባት፤ እሚታም ይሁን ታላቅ እህት እና ወንድም ጸጸቱ እስከ መቃብር ይሆናል። ስለቻሉ ኃላፊነታቸውን የተወጡ ምሩቃን በምህረት ቅድስና የመኖር ዕድል ይኖራቸዋል። ግን ሁልጊዜ ለልጆች የወላጆች መኖር #ትርታቸው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። መኖር #ካንፓሳችን ነው። መኖርም #ኮንፓሳችን ነውና።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
20.12.2025
መኖራችን ካንፓሳችን፤ ኮንፓሳችንም።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ