ደግነት እራሱን በታምር #እያዳነ በእናት አገሬ ኢትዮጵያ እንሆ አየሁኝ።

 

ደግነት እራሱን በታምር #እያዳነ በእናት አገሬ ኢትዮጵያ እንሆ አየሁኝ።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 May be an image of one or more people and text
 
"እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል። ሰው ግን አያስተውለውም።"
 
#ምክንያት ተሰጥቶናል እና ከደግነት ከእራሱ እንማር። 
 
አባ ቅንዬ፤ አባ የደግነት አባት መታመሙን ከገለጸበት ደቂቃ ጀምሮ ደግነት ልቦናችን #አህቲ አድርጎ ትውልዱን ሲንከባከብ፤ ሲመራም አየሁኝ። 
 
ባለፈው ሰሞን የቲክቶክ ሽልማት ላይ ከአንገት በላይ ስፔሻሊስቱ ዶር አብይ ታደሰ ይሸለማል፤ እሱ ሽልማቱ ለእኔ ሳይሆን ለፓስተር አብነት ይሰጥልኝ አሉ፤ ፓስተር አብነት ደግሞ ከእኔ በላይ መልዕክተኛው አለ እና ለእሱ ይሰጥልኝ አሉ። ሦስቱ አንድ መድረክ ላይ ኢጎን እንኩትኩት አድርገው አድቅቀው መድረክ ላይ ታዩ። ልጽፍበት ሁሉ አስቤ ለእናት ክብር አዳልቼ ጊዜየን ለእናት መገብኩኝ። ፎቶው ግን ስክሪን ላይ ያነሳሁት ጥራት ቢጎድለውም አለኝ። 
 
ትውልዱ አሻም ያላቸው ትርኪምርኪ ትርምስምሶች ሳይ ልቤ በተስፋ ይሞላል። አንዲት ደረቅ የፕላስቲክ አበባ ሲሰጥ ለሚንገረግባቸው ትውልዱ እንዲህ በአደባባይ ወስነው ሆነው የሚገኙበት የመከባበር አድማስ #ስደት ላይ በመሆኔ ቀረብኝ የምለውን የውስጤን መሻት ወጣቶች ሁነውበት ሳይ እንኳንም አልሞትኩኝ፤ ትንሽ መሰነባበቴ ለካስ ለበጎ ነው እላለሁኝ። 
 
የእኛ ትውልድ በማርክሲስት ሌኒኒስት ፍልስፍና በዘራብን አረም #የተበከለ ነው። ሳዝንም ኑሬያለሁኝ። አሁን ግን #መካሻ እያገኜሁ ነው።
በትውልድ ላይ የሚሠሩ ግሎባል ላይም፤ አገሬ ላይም ያሉ ፕሮጀክቶች እከታተላለሁኝ። እና ትውልድ ለደግነት #ወረፋ ሲይዝ ሳይ ጤናየንም አገኛለሁኝ።
 
ሳልችል ስቀር አቅመ ቢስነት ይሰማኛል። ማዳን መቻል መታደል ነው። እነኝህ ወጣቶች ለእኔ #ሐዋርያ ናቸው። ብልጠትን፤ መኮፈስን፤ ክብርን አሻም ያሉ ፈርጦች። 
 
#ምልሰት ስለ ደግነት አባት፤ አባ ቅንዬ ልመለስ።
 
የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ #እህቶቻችን ዕንባቸውን ማቆም አልቻሉም። የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ወገኖቻችን "ልብ ነው እምትፈልገው ወይንስ ኩላሊት የምትፈልገው እኔ ልሰጥህ ዝግጁ ነኝ" ይላል ወጣቱ። 
 
ደግነት እራሱን በታምር እያዳነ መሆኑን ተመለከትኩት። ከደስታ በላይ ሐሴት አገኜሁኝ። በውነቱ አምላኬንም አመሰገንኩኝ። ይገባልም። እኔ ጉዳዬ #ትውልዱ ነው። በቃ ሌላ ጥሪ የለኝም።
 
በሚዲያ የምናውቀው አቶ ሞጣ እራሱ በፓስተር አብነት ህመም ከውስጡ #ማዘኑን ሳደምጥ የደግነትን #አይበገሬ አቅም አየሁኝ።
ፓስተር አብነት በአገራችን በገጠመው የመሬት መንሸራተት ምክንያት #ተቋም ሆኖ አሳየን። እኔ ያወቅሁት የዛን ጊዜ ነበር። 
 
እኔ የኢትዮጵያ ፓርላማ የሚባለው እንዲህ ዓይነት #ደጋግ ሰብዕናወች በአሃቲ ልቦና የሚገኙበት እንዲሆን ልቤ ይፈልጋል። "የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፤፦እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።" 
 
ምኞቴ ኢትዮጵያን #በኦርጋኒክ ተፈጥሮዋ ልክ የሚመራ ህግ #አውጪ፤ ህግ #ተርጓሚ እና ህግ #ፈፃሚ እንዲኖራት ነው እምመኜው።
የተሰጣቸው ስለደግነት፤ ስለተስፋማነት ለትውልዱ ሽልማት ናቸው። ሰው መሆንን የተቀበሉ፤ ያከበሩ - የሰውኛ ማህበርተኞች ሥልጣን፤ ሹመት፤ ፋክክር፤ ቅናት ማጣጣልን #አክ የሚሉ ሁሉም ወገናቸው፤ ሁሉም የመኖራቸው ትርጉም ይሆን ዘንድ ለዚያ እንዲያበቃቸው እመኛለሁ። እሻለሁኝ።
 
ፓስተር አብነት መጨነቃችን እራሱ ከበደው። ደግነቱ ያስተማራቸው ደግሙ ተጨነቁ፤ አለቀሱ፤ እራሳቸውን ለመስጠት የወሰኑ መኖርን የጀመሩ ናቸው። በውነትም የሰለጠኑ ናቸው። ጭካኔ እኮ የስልጣኔ ጉድለት ነው። 
 
የሆነ ሆኖ መኖሬ ኑሮ በዘመኔ ይህን እንዳይ ለፈቀደልኝ አምላኬ ለልዑል እግዚአብሄር ምስጋና ይግባው። አሜን።
 
1) ደግነት ዞግ የለውም።
2) ደግነት ክልል አያውቅም።
3) ደግነት ፆታ የለውም።
4) ደግነት የቆዳ ቀለም የለውም።
5) ደግነት የዕውቀት የዲግሪ ደረጃ አይጠይቅም።
6) ደግነት የሃብት ደረጃ ትዝብሎት አያውቅም።
7) ደግነት የክት እና የዘወትር የሚል ልዩነት አያውቅም።
ስምንት) ደግነት ቂም ስለመፈጠሩም አያውቅም።
9) ደግነት በቀል የሚባል አጥፊ መዶሻ በምድር መኖሩን አያውቅም።
10) ደግነት ሁሉን ይወዳል - በእኩልነት።
11) ደግነት ሁሉን ያከብራል - በነፃነት።
12) ደግነት ሁሉን ይችላል - በደግነት።
13) ደግነት ሁሉን ይቀበላል - በፈጣሪ እርዳታ።
14) ደግነት ሁሉን መከራ ይሸከማል በአማኑኤል እርዳታ።
15) ደግነት ከእሳት ያወጣል በአምላኩ - ጥበብ።
16) ደግነት ምድር ከምታውቀው የጥበብ ሞራል በላይም ነው።
 
ታናሽ ወንድሜ ፓስተር አብነት የደግነት #ሐዋርያነቱ #ስላሰበለ ተመስጋኙ አምላካችን፤ አላሃችን ነው። በሽተኞች አሉ። ይህን ጹሁፍ ለማሳመም ይህ አለ፤ ያ አለ እያሉ የሚያውኩ። ጎንደሬወች ባለ ቅኔ ናቸው። " ሸማ በየዘርፋ ይለበሳል" ይላሉ።
 
ከማይገናኝ አጀንዳ ጋር እያገናኛችሁ ብጥበጣ ለሚያሰኛችሁ ይህ ቤት ልካችሁ አይደለምና በፈቃዳችሁ ወስኖ አለመገኜት ይቻላል።
እኔ ፍጥረተ ነገሬ ለጭካኔ አልተፈጠረም። ከ15 ዓመታት በፊት ነው ተመድን፤ አውሮፓ ህብረትን የሞገትኩት። መልሳቸውም በእጄ ላይ ይገኛል። የዓለም ቀውስ እኮ #ምንጩ አንድ ነው። #መፍትሄውም አንድ ነው። ዓለማችን በወሳኝ የፍቅር ተፈጥሮ፤ የህግ ፍልስፍና ተግታ ብትሠራ። በቃ የተደላደለ የሰላም ዓውደ ምህረት መሆን ትችል ነበር።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
18/12/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።