የፖለቲካ እስረኞች ወገኖቼ #አዋን ይፈቱልኝ፤ በእስር ቤት እያሉ ወገኖቼ ጤናቸው ይጠበቅልኝ እንጂ አይደለም በአክብሮት እና በትህትና #ተንበርክኬ ብለምን የሚቀርብኝ ቅርጥፍጣፊ ክብር የለም።
የፖለቲካ እስረኞች ወገኖቼ #አዋን ይፈቱልኝ፤ በእስር ቤት እያሉ ወገኖቼ ጤናቸው ይጠበቅልኝ እንጂ አይደለም በአክብሮት እና በትህትና #ተንበርክኬ ብለምን የሚቀርብኝ ቅርጥፍጣፊ ክብር የለም።
#ምዕራፍ ፲፯
እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ገና በጋሜ እና ታሬዬ ዘመን ጀምሮ ተከብሬ ነበር በፖለቲካ ተግባር ተኮትኩቼ ያደግኩት። እንደዛሬው ማህበራዊ ሚዲያ ቢኖር ከቶፕ ሁለገብ፤ ተከባሪወች እና ተወዳጆች መሃል የመሆን ዕድሉ የነበረኝ ሴት እሆን በነበረ።
ለእኔ የሙያ ብቃት፤ የሥራ ትጋት እና ቅልጥፍና ያግዛሉ በተባሉ መድረኮች ሁሉ እማርበት ዘንድ ሙሉ የዕድል በር የተከፈተልኝ ወጣት ነበርኩኝ። በእኔ ዘመን ዕንቁ ሴት ወጣቶች በርከት ያልን ነበርን። ከሁሉም ግን ለእኔ ይሰጥ የነበረው አትኩሮት እና፤ በእኔ ይጣል የነበረው ተስፋ ሰፊ ነበር።
ሁሉንም የክብር አይነት አውቀዋለሁኝ። ለዚህም ነው ለውዳሴ፤ የማይደንቀኝ የማልንደፋደፈው ለጭብጨባ ሆነ ተከታይ ለማበራከት። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ብርቱ ናቸው ብዬ ለማምናቸው በገፍ የሰብዕና ግንባታ፤ ምስክርነት በቅንነት የመስጠት አቅሜም ምንጩ ይኽው ነው። በብዙ ሰው ድጋፍ ላይ ቁብ የለ ሰብዕና ስለአንድ ሰው ሰብዕና የመመስከር #አቅም የለውም። ለምን? ከእነሱ የተሻለ ሰብዕና እንዲወጣ ስለማይፈለግ።
እኔ በምን ሁነት የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ዘንድ እተጋ እንደነበር በዓለም ውስጥ ያሉ ዕምነት ጥዬ አቤቱታ ያቀርብኩባቸው መንግሥታት፤ ተቋማት ሊቀ - ሊቃውንታት ያውቁታል።
በምድር ውስጥ እኔ በምፈጽመው ልክ ጭንቅ፥ ጥብብ ብሎ ካቴና ውስጥ ውለው ለሚያድሩ ወገኖቹ የተጋ እንብዛም ነው። የጭብጨባ ኳኳቴ ስለማልፈልግ ነው "ሙያ በልብ" ጉዳዩ የሆነው። በብዙ ተግቻለሁኝ። አሳክቻለሁም። ዕድሜ ለቲም ገዱ እራሱንም ሳያተርፍ ከነበለው እንጂ። የተገኜው ዕድል ሰማያዊ ነበር።
የሆነ ሆኖ ለተፈጠርኩበት የጥሪ ጸጋዬ #የባከነ ጊዜ በህይወቴ የለም። የትኛውም እስረኛ ከእስር ከተፈታ በኋላ ግን እናመሰግናለን ሲል ሰምቼ አላውቅም። ከእነ መፈጠሬም አያውቁኝም። መንፈሴ ብቻ ሳይሆን ያለኝን በማካፈልም እተጋለሁኝ። ግን የውዳሴ አታሞ መለከት እንዲነፋልኝ አልሻም።
#የምፈልገው አምስት ነገር ብቻ ነው።
1) ከካቴና የወጡ ወገኖች የትግል ስልታቸው #በታረመ አንደበት እንዲሆን እሻ ነበር።
2) ከእስር መልስ #ጥሞና ይወስዱ ዘንድ ምኞቴ ነበር።
3) ተው አያዋጣም ብዬ የምጽፈው ተነቦ "ላም እረኛ ምን አለ" ሊደመጥ ይገባ ነበር።
4) የሚፈሰው አቅም #ወጪ መሆኑ ከልብ ሊታሰብበት ይገባ ነበር።
5) መስዋዕትነት በእጅጉ #የቀነሰ ትግል መምረጥ ይገባ ነበር።
እኔ ሥሰራ የእናት ፍቅር እና ስስትን፤ የእህት የወንድም ናፍቆትን፤ የአገር ትዝታ #ባን አድርጌ ነበር። አስቀድሜ የምሰራበት ዘርፍ የድምጽ አልባወቹ የኢትዮጵያ እናቶች #ዕንባን ነው። የኢትዮጵያ እናቶች የውስጥ ሰላም ማጣት የእኔ ጉዳዬ ነው። ስለሆነም እራሴን ማግጄ የቤተሰቦቼን ናፍቆት ገፍቼ እሰራለሁኝ። ምክንያቱም ለተጨማሪ ወገን ችግር መፍጠር መንገዴ ስላልሆነ።
ይህን መሰል እርምጃ የሚወስድ #ቆራጥ ሰብዕና ያስገኜው ስኬት እንደ ወንዝ ዳር አሽዋ ዋጋ ቢስ ሲሆን ነው የተመለከትኩት። የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ይህን የመሰለ መከራ እንዲያስተናግድ የሆነው #አድማጭ ጠፍቶ ነው። መደማመጥ ቢኖር በርከትከት ያሉ ቀና እና ቅን መንገዶች ነበሩ።
በሚሳኤል #እሩምታ አልነበረም ህወሃት ፈቅዶ፤ እራሱም ተወዳድሮ ሥልጣነ መንግሥቱን ያስረከበው። በትህትናዊ፤ አክብሮታዊ፤ አትኩሮታዊ ተከታታይ ትጋት ነበር ታምር የተሰራው። ያን ክስተት በጥንቃቄ፤ በመመካከር፤ በመደማመጥ በቅንነት ማስተናገድ መምራት ሲገባ እልህ፤ ቁጣ፤ ብስጭት፤ ዘለፋ፤ ከፍ ሲልም #ቀልኃ ተመረጠ።
ብዙ በጣም ብዙ ዕንቁ ወንድሞች፤ እህቶች አጣን። ብዙም ለካቴና ተዳረገ። የአማራ ህዝብ፤ የትግራይ ህዝብ፤ የኦሮሞ ህዝብ፤ የአፋር ህዝብ፤ የአዲስ አበባ ህዝብ ስቃያቸውን፤ አሳራቸውን ያዩት መደማመጥ ተሰዶ ነው። ሌላው የሚገርመኝ ይሉኝታ ቢስነት ደግሞ ሁልጊዜ ለእኔ የሰብእና ግንባታ፤ ክብር እና ልዕልና ተገበሩልኝ መቢሉ ነው። #ሁልጊዜ????
በሌላ በኩል የእኔ ትግል በፍጹም ኢትዮጵያ ውስጥ #የፖለቲካ #እስረኛ እንዳይኖር ነበር። ለጥቂት ቀን እፎይ አልን 2010 እኢአ። ከዛ ቀጠለ። የሆነ ሆኖ #የማርበርግ በሽታ ወረርሽኙ ካሰጋቸው ኢትዮጵያዊ ዜጎች አንዷ እኔ ነኝ። ከሁሉም ለእስረኞች፤ ለተማሪወች። ስለዚህ አቤቱታዬን ለክብርት ዶር መቅደስ ዳባ የጤና ሚኒስተር አክብሬ ማቅረቤ የጎረበጣቸው ወገኖቼ ተበሳጭተዋል።
አንድ ሰው አቤቱታ ሲያቀርብ #በግልምጫ፤ በትምክህት፤ በማናኽሎኝነት ሊሆን ፈጽሞ አይገባም። ይህን መስመር ተከትሎ የሚገኝ ፖለቲካዊ ትርፍ፤ ማህበራዊ ትርፍ ፈጽሞ የለም። አማራጭ ከኖረ እስኪ ካቴና ላይ ላሉ ወገኖቻችን ይድረሱላቸው ሲታመሙ????
አጉል በሌለ አቅም ላይ ከመኮፈስ በስተቀር ፤ ምንም አማራጭ ሳይኖር ያዙኝ ልቀቁኝ #ሙት መሬት ነው። እወነቱን ብነግራችሁ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኛ እንዳይኖር ለማስወሰን ማንኛውንም አካል #ተንበርክኬ፤ #የእንብርክክ እየሄድኩኝ ብለምን የሚቀርብኝ የክብር ቁርጥራጭ የለም።
እግዚአብሄር አምላክ ከፍጥረታቱ ሁሉ አክብሮ፤ ቀድሶ እና መርቆ የፈጠረኝ የሰው ልጅ ነኝ እና። ስፈጠር እኮ ተከብሬ ነው። በአንድ ሰዓት ውስጥ መንበር ላይ፤ በደቂቃወች ውስጥ ትቢያ ላይ እንኩትኩቱ የሚወጣ ሰውሰራሽ ክብር ትዝብሎኝ አያውቅም። ወደፊትም አይናፍቀኝም። ህልሜ እና ምኞቴ ሰው ባስተሳሰቡ፤ ሰው በአመለካከቱ፤ ሰው በተቋሙ ሰላማዊ ጉዞ እቀባ፤ እገታ፤ እንግልት አይድረስበት ነው የእኔ የትግል መስመር።
ታጋዩም ጋዜጠኛ፤ አክቲቢስት፤ የፖለቲካ ተንታኝ፤ ዩቲወበር፤ ቲክቶከር፤ ብሎገር፤ የፖለቲካ መሪም ፍላጎቱን ለማሳካት ሃይማኖት መኖሩ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖቱ በሚፈቅደው ዶግማና ቀኖና በታረመ አንደበት፤ ህግ ሳይተላለፍ፤ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ጥያቄውን፤ ሙግቱን ሊያቀርብ ይገባል።
በሌላ በኩል እሱ ትህትናው ከተሰደደ የእኔ ትህትና እንዲሰደድ መናፈቅም ከንቱነት ነው። እኔን መጫን አይፈቀደምም። እኔን እንደ ቦይ ውሃ አቅጣጫ መምራትም አይቻልም። እንደምፈልገው በራሴ አርት የመታገል ሙሉ መብት አለኝ። ጠብ ፈጽሞ አልወድም። ግጭትም አይናፍቀኝም። ሰው መናቅ ፈጽሞ አይታሰብም። አናንቄ፤ አጣጥዬ እምወጥነው የሥራ ዘርፍም ኑሮ አያውቅም።
ለወደፊትም የሰውን ልጅ፤ ተፈጥሮን አክብሬ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ የሃሳብ ሙግቴ ይቀጥላል። የራሴ አለቃ እራሴው ነኝ። የየትኛውም ተቋም፤ የፖለቲካ ድርጅት አባል አይደለሁም። አካልም አይደለሁም። ወደፊትም አልሆንምም። የእራሴ አቋም እና አሻራ ያለኝ ሴት ነኝ። እራሴን አፍርሼ ከአዳዲስ ቱማታ ሃሳብ ጋር እፍ ስል አልገኝም። በሌላ በኩል ሲሰራ እና ሲፈርስ ውሎ በሚያድር፤ ሲናድ እና ሲገናኝም ውሎ በሚያድር፤ ሰርክ በአንጃ በሚንቆጠቆጥ ደራሽ ሁነት ውስጥ የእኔ ሰብዕና ታዳሚ ከቶውንም፤ መቸውንም አይሆንም። ከአዘኑት፤ ከተጎዱት፤ ከሚያለቅሱት ወገኖቼ ጎን መቆሜ ግን ይቀጥላል።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
10/12/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ለሰው ልጅ እና ለተፈጥሮ ያለኝ አክብሮት የጸና ነው!

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ